መረጃዎች | 11ኛ የጨዋታ ቀን

የሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛ ዕለት ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን እኛም ሁለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን በተከታዩ ፅሁፍ አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

ሁለቱን አዲስ አዳጊዎችን የሚያገነኘው የምሳ ሰዓት ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በተሻለ መነሳሳት ላይ ሆነው የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሆነ ይታመናል። ኢትዮጵያ መድኖች እጅግ አሰቃቂ ከነበረው የመጀመሪያ ጨዋታ ሽንፈት ማግስት በሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ግቦች ሲያሸንፉ በአንፃሩ ለገጣፎ ለገዳዲዎችም ምንም እንኳን በመጨረሻው የድሬዳዋ ጨዋታ ግብ አስተናግደው አቻ ቢለያዩም ከሁለት ጨዋታዎች የሰበሰቡትን አራት ነጥብ ለቡድኑ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።

መድኖች አሁንም የተከላካይ መስመራቸው በጉዳት መታመሱን ቢቀጥልም በነገው ጨዋታ አዎንታዊ ውጤት ይዘው ለመውጣት ጥንቃቄ ላይ መሰረት ያደረገን አቀራረብ እንደሚከተሉ ሲጠበቅ የሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም በሁለቱ መስመሮች የሚጫወቱት ኪቲካ ጀማ እና ብሩክ ሙሉጌታ ለመድኖች በማጥቃቱ ረገድ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብለው ይጠበቃሉ።

እንደ ቡድን በመከላከል ሆነ በማጥቃት ለመጫወት ጥረት የሚያደርጉት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በተለይ ወደ ማጥቃት በሚያደርጓቸው ሽግግሮች አብዝተው ረጃጅም ኳሶችን ለካርሎስ ዳምጠው ከመጣል ባለፈ አማካዩ ተፈራ አንለይ ቡድኑ በቅብብሎች መሀል ለመሀል ማጥቃት የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር የሚያደርገው ጥለት ለቡድኑ ተጨማሪ ገፅታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አሁንም በተከላካይ መስመር ጉዳት እየታመሱ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች በነገውም ጨዋታ እንዲሁ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ተመስገን ተስፋዬ ፣ ፀጋሰው ድማሙ በጉዳት እንዲሁም ጋናዊውን ሀቢብ መሐመድ ደግሞ ባልተጠናቀቀ የወረቀት ጉዳይ መጠቀም የማይችሉ ሲሆን የወረቀት ጉዳዩ የተጠናቀቀው ዩጋንዳዊው ሳይመን ፒተር ደግሞ መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ ከነገው ስብስብ ውጭ ሆኗል። በተቃራኒው በአሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ የሚመሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ደግሞ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብን ይዘው ለነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በነገው ዕለት የሚያደርጉትን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ባህሩ ተካ ሲመራው ረዳቶቹ ደግሞ ሲራጅ ኑርበገን እና ወጋየሁ አየለ ሲሆኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ይሆናሉ፡፡

ሀዋሳ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥባቸውን በሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት በርከት ያለ ደቂቃዎችን ከኳስ ውጪ በማሳለፍ ያሳኩትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊነታቸውን ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉበት ይጠበቃል።

ሀዋሳ ከተማ ምንም እንኳን በመጀመሪያው ጨዋታ ያልተጠበቀ ሽንፈት ቢያስተናግዱም በሁለተኛው ጨዋታ በአስገራሚ የመከላከል አደረጃጀት ለኢትዮጵያ ቡና ኳሱን ለቀው በመጫወት ወሳኝ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል። በነገው ጨዋታ አዎንታዊነትን ጨምሮ እንደሚቀርብ የሚጠበቀው ቡድኑ ይበልጥ በነፃነት እንደሚጫወት ይገመታል። በጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች አሁንም ያለ ተከላካያቸው በረከት ሳሙኤል የሚቀርቡ ሲሆን ይህም ጨዋታ በቅጣት ሳቢያ የሚያመልጠው የመጨረሻ ጨዋታ እንደሆነ ታውቋል።

ከመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት መልስ መቻልን ፍፁም ከተለየ የሜዳ ላይ ታታሪነት ጋር ያሸነፉት አዳማ ከተማዎች ይህን የትጋት ደረጃ በቀጣይነት ማስቀጠል ከቻሉ ከጨዋታዎች ውጤትን ይዘው ለመውጣት የሚቸገሩ አይመስሉም። በተለይም አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ቡድኑ ከኳስ ውጭ በሚሆንባቸው ቅፅበቶች በጥልቀት እየተሳበ በመመለስ ይረዳበት የነበረው መንገድ የተለየ የነበረ ሲሆን ይህን ሂደት ነገም ያሳዩን ይሆን የሚለው ነገር ይጠበቃል። በአዳማ ከተማዎች በኩል በቅጣትም ሆነ ጉዳት ነፃ ስብስብን ይዘው ይቀርባሉ።

ተጋጣሚዎቹ እስካሁን ድረስ በሊጉ 41 ጊዜ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች 92 ግቦች ሲመዘገቡ 48 በሀዋሳ ከተማ 44 ደግሞ በአዳማ ከተማ ስም ተቆጥረዋል። ሀዋሳ 18 አዳማ ደግሞ 11 ጊዜ ድል ሲቀናቸው በቀሩት 12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ መልስ ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነቱ ሲሰጠው ፣ ሠለሞን ተስፋዬ እና ሻረው ጌታቸው ረዳቶች እንዲሁም ኤፍሬም ደበሌ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ለጨዋታው ተመርጧል፡፡