ኢትዮጵያ መድን አብሮት ወደ ሊጉ ያደገውን ለገጣፎ ለገዳዲ 4ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ባሳለፍነው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን ከመመራት ተነስተው ያሸነፉት ኢትዮጵያ መድኖች በዛሬው ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ተካልኝ ደጀኔን በሳሙኤል ዮሐንስ እንዲሁም ተመስገን ተስፋዬን በባሲሩ ዑመር ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተቃራኒው የለገጣፎው አሠልጣኝ ጥላሁን ተሾመ ግን ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ ለአንድ የተለያየውን የመጀመሪያ አሰላለፍ ሳይቀይሩ ጨዋታውን ጀምረዋል።
ኳስን በራስ ቁጥጥር ስር ለማድረግ መሐል ሜዳ ላይ በነበረ ፍልሚያ ታጅቦ የጀመረው ጨዋታ ገና በ9ኛው ደቂቃ ግብ አስተናግዷል። በዚህም በአርባምንጩ ጨዋታ በተቆጠሩት አራቱ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው ኪቲካ ጅማ በተከላካዮች መሐል ወደ ፊት የላከውን ኳስ ሀቢብ ከማል በግራ እግሩ ግብ አድርጎታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ለዚህ ጎል መገኘት መነሻ የሆነው ኪቲካ የመሐል አጥቂው ብሩክ ሙሉጌታ ከግራ የሳጥኑ ክፍል መሬት ለመሬት ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ ዒላማውን ስቶበታል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ መጣር የጀመሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በረጃጅም እና የቆሙ ኳሶች ግብ ለማግኘት መንቀሳቀስ ይዘዋል። በ16ኛው ደቂቃ ደግሞ ተፈራ አንለይ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ አቡበከር ኑሪን ፈትኖ ተመልሷል። ከደቂቃ በኋላ ግን በተከላካዮች እና ግብ ጠባቂ አለመግባባት ስህተት ብሩክ ሊቀጣቸው ተቃርቦ ነበር። ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ እየቃኙ የነበሩት መድኖች በ22ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። በዚህም ወደ ግራ ካደላ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ሲያሻማው ለቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን እያደረገ የነበረው ባሲሩ ዑመር ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ደካማ የነበሩት ጣፎዎች በ30ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ለመጠቀም ጥረው ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም የግራ መስመር ተከላካዩ ኪሩቤል ወንድሙ ያሻገረውን ኳስ ቁመታሙ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው በግንባሩ ሞክሮት ሁለቱ የግብ ቋሚዎች ኳሱን ከግብነት አግደውታል። አጋማሹ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ አካፋይ ሰከንድ ላይ ደግሞ አንዋር ከመስመር ሌላ ኳስ አሻግሮ ዳዎት ቀለመወርቅ በተመሳሳይ በግንባሩ ወደ ግብ ልኮት ለጥቂት ወጥቶበታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በአደገኛ እና ወሳኝ ቦታዎች ብልጫ የተወሰደባቸው ጣፎዎች በቀጣዩ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመጠኑ ሻል ብለው የቀረቡ መስሏል። ገና አጋማሹ በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃም ካርሎስ ዳምጠው ኳስ ወደ ግብ ሲመታ ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ በእጅ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ኪሩቤል ወንድሙ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን መዘወር ያልቸሉት መድኖች ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ጥረዋል። በተቃራኒው በቶሎ ግብ ያስቆጠሩት ጣፎዎች ኳሱን ቢቆጣጠሩም ችኮላ በተሞላበት ለማጥቃት መጣራቸው እምብዛም ውጥናቸው እንዳይሰምር ሲያደርግ ታይቷል። ግብ ካገኙ በኋላም ቀጣዩን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት በ67ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም ካርሎስ ዳምጠው ከርቀት አክርሮ በመምታት ቡድኑን አቻ ሊያደርግ ነበር።
ጨዋታው 74ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የአሠልጣኝ ገብረመድህን ተጫዋቾች ሦስት ነጥቡን በአስተማማኝ ሁኔታ ያገኙበትን ሦስተኛ ጎል አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሳጥን ውስጥ መዝገቡ ኪቲካ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ አልቢትር ባህሩ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተው አምበሉ ሀብታሙ ሸዋለም አጋጣሚውን ግብ አድርጎታል። ከሦስተኛው ጎል በኋላ የወረዱት ጣፎዎች በ85፣ 88 እና 91ኛው ደቂቃ ኪቲካ እንዲሁም በ87ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አሚር ሙደሲር ተከታታይ ጥቃቶችን ሰንዝረውባቸው ነበር። ሙሉ የጨዋታ ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃም ሌላኛው ተቀይሮ የገባው እዮብ ገብረማርያም የማሳረጊያ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 4ለ1 ተጠናቋል።
ተከታታይ ድል ያገኙትን ኢትዮጵያ መድን የሚመሩት አሠልጣኝ ገብረመድህን ጎሎችን አስቆጥረው ቢያሸንፉም በእንቅስቃሴ ረገድ ቡድናቸው ገና በሚፈልጉት መንገድ እንዳልሆነ በማንሳት መሐል ሜዳውን በመቆጣጠር የጣፎን ወሳኝ ተጫዋቾች ለመቆጣጠር ያደረጉት ነገር ስኬታማ እንደሆነላቸው ከጨዋታው በኋላ ተናግረዋል። አሠልጣኝ ጥላሁን በበኩላቸው ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ አጥቅቶ ለመጫወት ቢያስቡም ተጫዋቾቹ ላይ የታየው ጉጉት ከኋላ ክፍተት ፈጥሮባቸው ግቦች እንዲቆጠሩባቸው እንዳደረገ በመግለፅ በቀጣይ ጨዋታ ክፍተታቸውን አሻሽለው እንደሚመጡ ገልፀዋል።