የሲዳማ ቡና ዋና አሠልጣኝ እና የቡድን መሪው በክለቡ ቦርድ ጥሪ ነገ ወደ ክለቡ መቀመጫ ከተማ ያመራሉ።
የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በባህርዳር ከተማ ከጀመረ እነሆ የሦስተኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ ደርሷል፡፡ በውድድሩ ላይም እየተካፈሉ ካሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ ቡና በሊጉ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 2ለ2 አቻ፣ በሀድያ ሆሳዕና 4ለ1 ሽንፈት እንዲሁም በትላንትናው ዕለት ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ 5ለ1 ተረቶ ማግኘት ከሚጠበቅበት ዘጠኝ ነጥብ አንዱን ብቻ አሳክቶ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዚህም የተነሳ የክለቡ የቦርድ አካላት በውጤቱ ደስተኛ ባለመሆናቸው ለአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ እና ለቡድን መሪው አቶ አሸብር ጥሪ ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡ ክለቡን ከዚህ ቀደም በተጫዋችነት ባሳለፍነው ዓመት በረዳት አሰልጣኝነት ዘንድሮ ደግሞ በዋና አሰልጣኝ ኃላፊነት የተረከቡት አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ከወቅታዊ ውጤት መጥፋት ጋር በተገናኘ የክለቡ ቦርድ በዛሬው ዕለት ጥሪ በማስተላለፍ ከቡድን መሪው አቶ አሸብር ጋር ወደ ሀዋሳ እንዲያመሩ ጥሪ የቀረበ ሲሆን አሠልጣኙ እና ቡድን መሪው ነገ ረፋድ ወደ ሀዋሳ ጉዞ እንደሚጀምሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአሰልጣኙ ቀጣይ እጣ ፈንታን በተመለከተ አሁን በግልፅ የሚታወቅ ነገር ባይኖረውም ነገ 8 ሰዓት ላይ የክለቡ ቦርድ ከአሰልጣኙ እና ቡድን መሪው ጋር ውይይት ለማድረግ በማሰብ ጥሪው እንደተላለፈ ዝግጅት ክፍላችን አውቃለች፡፡