ብዙም የጎል ሙከራዎችን ያላስመለከተን ቀዝቃዛው ጨዋታ በአዳማ ከተማ አሸነፊነት ተጠናቋል።
ከቀናት በፊት ከኢትዮጵያ ቡናን የረቱት ሀዋሳዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት ስብስብ ላይ ሰለሞን ወዴሳ፣ አዲሱ አቱላ ፣ ኢዮብ አለማየሁን አስወጥተው በምትካቸው ላውረንስ ላርቴን እና ወንድማማቾቹ ብርሀኑ አሻሞና ኤፍሬም አሻሞ በመተካት ለጨዋታው ሲቀርቡ በአንፃሩ አዳማዎች በኩል መቻልን ካሸነፉበት ጨዋታ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ዛሬው ጨዋታ አምርተዋል።
ተቀራራቢ የተጫዋች ጥራት ባላቸው ቡድኖች መካከል የሚካሄደውን ይህ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት ጅማሮውን ሲያደርግ የጨዋታው የመጀመርያ ሃያ ደቂቃ ሁለት መልክ የነበረው እንቅስቃሴ ያስመለከተን ነበር። ተከታታይ የተሳኩ ቅብብሎችን ለማድረግ የተቸገሩት ሀዋሳዎች ከመከላከል ባለፈ ወደ ፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር የተቸገሩ ሲሆን በአንፃሩ አዳማዎች በጥሩ ቅልጥፍና ኳሶችን በሚገባ በመቀባበል የተጋጣሚን ግብ ለማግኘት የተሻለ ጥረት ቢያደርጉም ጥራት ያላቸውን እድሎችን በመፍጠር ረገድ ግን ውስንነቶች ነበሩባቸው።
ቀስ በቀስ በጨዋታው መሐል ሜዳ ላይ የበላይነት ለመውሰድ በሚደረግ ፍትጊያ የጨዋታው መንፈስ እየደበበዘዘ ቢሄድም በ35ኛው ደቂቃ ግን በጨዋታው የመጀመርያውን ግልፅ የጎል ዕድል አስመልክቶናል። አሌ ሱሌማን ከብርሀኑ አሻሞ የተቀበለውን ኳስ በጠንካራ የግራ እግሩ ወደ ጎል አክሮ የመታውን ኳስ አዲሱ የአዳማ ከተማ ግብጠባቂ ክዋሜ ባሀ እንደምንም አድኖታል።
በአፀፋው ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ አዳማዎች ከቀኝ መስመር ከደስታ ዮሐንስ የተሻገረውን ኳስ አብዲሳ ጀማል በግንባሩ ገጭቶ የግቡ ቋሚ ቢመልስበትም ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጭ አቋቋም በሚል ኳሷ ሳትፀድቅ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ካቆመበት በቀጠለው ሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደተቀዛቀዘ ብዙ የጎል ሙካራዎችን ሳያስመለክተን እስከ ስልሳኛው ደቂቃ ቢዘልቅም ካልተጠበቀ አቅጣጫ አዳማዎች የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አግኝተዋል።ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ከርቀት ዳዋ ሁቴሳ ወደ ጎል የመታውን ኳስ በሀዋሳ ተከላካዮች ተደርባ አቅጣጫዋን በመቀየር አላዛር ማርቆስ መረብ ላይ ማረፉን ተከትሎ አዳማዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
የዳዋ ሆቲሳ ጎል የጨዋታውን ሂደት ወደ መነቃቃት የቀየረች ስትሆን ከሦስት ደቂቃ በኃላ ሀዋሳዎች ከርቀት ያሻገሩትን የቅጣት ምት ኳስ አብዱልባሲጥ ከማል በግንባር በመግጨት የሞከረው ወደ ጨዋታው የወጣበት ሀዋሳዎችን በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ሙከራ ነበር።
ጨዋታው ወደ መጠናቀቁ ሲያመራ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾችን በማስወጣት የአጥቂ ቁጥራቸውን በማብዛት የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ግን ከፍላጎት የዘለለ አስደንጋጭ ሙከራን ሳያሳየን ቀርቷል። የአንድ ጎል መሪነታቸው በተወሰነ መልኩ ምቾት የሰጣቸው የሚመሰሉት አሰልጣኝ ይታገሱ ቡድናቸው ይበልጥ ወደ መከላከሉ አድልቶ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት በቅተዋል።
ሦስት ነጥብ ማግኘታቸው ቢያስደስታቸውም አሁንም የተሻለውን አዳማ ለማሳየት በማሸነፍ ውስጥ ቡድኑን እየሰሩ እደሚቀጥሉ አሰልጣኝ ይታገሱ ገልፀው በአንበላቸው ዳዋ ሁቴሳ እንቅስቃሴ ደስተኛ መሆናቸውን እንዲሁ ከጨዋታው በኃላ ሲናገሩ በሽንፈት የጨረሱት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ደግሞ ጎል እስከተቆጠረባቸው ደቂቃ ድረስ በእንቅስቃሴ ጨዋታው እንዳሰቡት የሄደ ቢሆንም ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ ክፍት የሜዳ ክፍል ሊያገኙ ባለመቻላቸው ውጤቱ ከእነርሱ እደራቀ ገልፀዋል።