ሦስተኛው የጨዋታ ሳምንት ነገ በሚያስተናግዳቸው ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰናድተናል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
የነገው የጨዋታ ቀን በሊጉ የግንኙነት ታሪካቸው ተመጣጣኝ ውጤት ሲያስመዘግቡ የቆዩትን ብርቱካናማዎቹን እና ነብሮቹን ያገናኛል። በዘንድሮው አጀማመራቸው ድሬዎች ሁለት የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግቡ በአንድ ነጥብ ብልጫ ያላቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ከመጀመሪያው ሽንፈት ያገገሙበትን አንድ ድል አሳክተዋል።
ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር 1-1 የተለያዩት ድሬዳዋ ከተማዎች አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ‘አለመረጋጋት’ ሲሉ የገለፁትን ችግር መቅረፍ ዋነኛ የቤት ሥራቸው ይመስላል። የተጋጣሚን ጥቃት በማቋረጡ በኩል የማያስከፋ ጊዜ የነበራቸው ድሬዎች ወደ ተጋጣሚ የአደጋ ክልል ሲጠጉ ያላቸው መናበብ የሳቡት ደረጃ ላይ የደረሰ አልሆነም። በአመዛኙ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ከሆነው የቀኝ መስመር የሚነሱ ኳሶች ነገም ዋነኛ የማጥቂያ አማራጮች እንደሚሆኑም ይጠበቃል።
ነገ ቁልፍ አማካያቸውን የማጣታቸው ነገር መሀል ላይ የሚፈጥርባቸውን ክፍተት የመድፈን ኃላፊነት ያለባቸው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ በቡድናቸው ማየት የሚፈልጉትን እንቅስቃሴ ያገኙ ይመስላል። ከወገብ በላይ የነበረው የማጥቃት ፍሰት በተለይም መሀል ለመሀል በሚሰነዘሩ ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች የተቃኘበት አኳኋን የነብሮቹ ጠንካራ ሆኖ የታየ ሲሆን ይህንን በወጥነት ማስቀጠል የመቻል ፈተናውም በነገው ጨዋታ የሚታይ ይሆናል።
ድሬዳዋ ከተማ የሁለት ጨዋታ ቅጣት የሚቀረው ኤልያስ አሕመድን ከማጣቱ በቀር ቀሪ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ቃለአብ ውብሸት ከጉዳቱ ሙሉ በሙሉ ሲመለስ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። ለቡድኑ መልካም በሆነው ዜና ጋናዊው ሪችሞንድ ኦዶንጎ እና ስቴፈን ኒያርኮ የመኖሪያ ፍቃድ አጠናቀው በነገው ጨዋታ ላይ ይሰለፋሉ፡፡
ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ የተመጣጠነ ውጤት ያስመዘገቡባቸውን ስድስት ጨዋታዎች አድርገዋል። በዚህም ዕኩል ሁለት ጊዜ በመሸናነፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ
ሆሳዕና 8 ድሬዳዋ ደግሞ 7 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ይህ የነገውን ቀዳሚ ጨዋታ በተካልኝ ለማ የመሀል ዳኝነት የሚከናወን ሲሆን ሙስጠፋ መኪ እና ወጋየሁ አየለ ረዳቶች ባህሩ ተካ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።
ወልቂጤ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ሲገናኙ ሜዳ ላይ ማራኪ ፉክክር እያስመለክቱትን ያሉት ሰራተኞቹ እና ቡናማዎቹ ነገ በሁለተኛው ጨዋታ ይፋለማሉ። የዘንድሮው የቡድኖቹ አጀማመር የተራራቀ ሆኗል። በዚህም ወልቂጤ ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን ሲያሳካ ኢትዮጵያ ቡና አንድ ነጥብ ይዞ ለነገው ጨዋታ ደርሷል።
ድል ያደረጋቸውን ሁለቱንም ጨዋታዎች በ1-0 ውጤት የፈፀመው ወልቂጤ ከተማ መንገዱን ለማስቀጠል እስካሁን ግብ ያላስተናገደበትን የመከላከል መዋቅር ለነገ ዋነኛ ትኩረቱ ሊሆን ይችላል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በመጨረሻው ጨዋታ አስተያየታቸውን ሲሰጡ የማጥቃት ሽግግር ላይ ትኩረታቸውን ማድረጋቸውን ስናነሳ ደግሞ የነገ ተጋጣሚያቸውን ጥቃት ከማፈን ባለፈ በቶሎ ወደ ግብ መድረስን ያለመ የጨዋታ ዕቅድ ሊኖራቸው እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ሀዋሳ ከተማ ላይ እንደገጠማቸው ዓይነት መከላከል በነገው ጨዋታ ላያገኛቸው ቢችልም ቡድኑ በተለይም ከወገብ በላይ ያለው የውህደት ደረጃ ተጋጣሚን ደጋግሞ በማስከፈቱ በኩል ብዙ እንደሚቀረው መታየቱ ዋነኛ የትኩረት ነጥቡ ይመስላል። አማካይ ክፍል ላይ በጨዋታው የሚኖረው ፍልሚያ ውጤቱን የመወሰን አቅም ቢኖረውም የተሻለ የግብ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን ቡናዎች ከአዲሶቹ አጥቂዎቻቸው የተሻለ አፈፃፀም የሚጠብቁበት ጨዋታም ይሆናል።
በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ተከላካዩ ገዛኸኝ ደሳለኝን በጉዳት ሲያጣ በወልቂጤ ከተማ በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና የለም።
ባለፉት ሁሉት ዓመታት ቡድኖቹ ከተገናኙባቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፍ ሲችል በአንዱ ነጥብ ተጋርተዋል። በአራቱ ጨዋታዎች 15 ጎሎች ከመረብ ሲዋሀዱ ዘጠኙ በኢትዮጵያ ቡና ስድስቱ ደግሞ በወልቂጤ ስም የተመዘገቡ ነበሩ።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ይህንን ጨዋታ ለመምራት ሲመደቡ ለዓለም ዋሲሁን እና እሱባለው መብራቱ በረዳትነት እያሱ ፈንቴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ኃላፊነት ወስደዋል