ሪፖርት | ነብሮቹ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል

የሦስተኛ ጨዋታ ሳምንት የመጨረሻ የጨዋታ ዕለት የመጀመሪያ በነበረው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ነጥብ የተጋሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት የመጀመሪያ 11 ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ብሩክ ቃልቦሬ እና ዮሴፍ ዮሐንስን አስወጥተው በምትካቸው አቤል አሰበ እና ያሬድ ታደሰን አስገብተዋል።  በአንፃሩ ሲዳማ ቡናን ረተው የመጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ሦስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ መሳይ አያኖ ፒፕ ሳይዱን ሲተካ ጉዳት በገጠመው ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን እና ራምኬል ሎክ ምትክ የመኖርያ ፍቃድ ጉዳያቸውን ከቀናት በፊት የጨረሱትን ስቲቨን ናያርኮ እና ሪችሞንድ አዶንጎን የመጀመሪያ ተሰላፊዎች በማድረግ ጨዋታውን ጀምረዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ አጀማመር በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች በመስመሮች እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ መሀል ለመሀል የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ቢመስልም የሁለቱ ቡድኖች የማጥቃት ጨዋታ ግን በእጅጉ ጥራት የሚጎድለው ነበር።

በጨዋታው ድሬዳዋ ከተማዎች አንፃራዊ የበላይነት የያዙ በመሰሉበት አጀማመር በ20ኛው ደቂቃ አብዱለቲፍ መሐመድ ወደ ቀኝ ካደላ ስፍራ ያሻማው እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበችበት የቆመ ኳስ አጋጣሚ እንዲሁም በ21 ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ከርቀት አክርሮ መትቶ ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ነገር ግን በ25ኛው ደቂቃ ላይ በሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል ከመሀል መነሻውን ባደረገ የማጥቃት ሂደት በጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን በጠበቀ ሙከራ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ባዬ ገዛኸኝ ያሻማውን ኳስ ለመያዝ ፍሬው ጌታሁን ግቡን ለቆ በመወጣበት ሂደት የመሀል ተከላካያቸው አሳንቲ ጎድፍሪ ይህን እንቅስቃሴ ሳይመለከት ኳሷን በጭንቅላቱ ገጭቶ ለማራቅ የሞከረውን ሳጥን ጠርዝ አካባቢ ይገኝ የነበረው እና የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ስቲቨን ናያርኮ በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር ሀዲያን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው ከወትሮው በተለየ አደራደር የቡድኑን የኳስ ቁጥጥር ሆነ የኳስ ዕድገት ለማሻሻል አቤል አሰበ እና ጋዲሳ መብራቴን በመሀል አማካይነት የተጠቀሙት ድሬዳዋ ከተማዎች በፍጥነት ኳሶችን ወደ መስመር እያወጡ ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም በተለይ ወደ ሳጥን የሚያሿማቸው ኳሶች ከጥልቀት የሚላኩ በመሆናቸው ድሬዎች እነዚህን ኳሶች ሳጥን ውስጥ በቁጥር በዝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

በጨዋታው ቀዳሚ መሆን የቻሉት ሀዲያዎች ከግቧ መቆጠር በኋላ በሂደት ይበልጥ ወደ ጨዋታው በመግባት የኳስ ቁጥጥር ድርሻቸውን ቢያሳድጉም በማጥቂያው ሲሶ ላይ ግን በተደጋጋሚ መገኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ42ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች በተመሳሳይ በመጀመሪያው ዒላማውን በጠበቀ ሙከራቸው አቻ መሆን ችለዋል። አቤል አሰበ በግሩም ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ቻርልስ ሙሴንግ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የላካት ኳስ ድሬዎችን አቻ አድርጋ ሁለቱ ቡድኖች በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ቢኒያም ጌታቸውን አስወጥተው በምትኩ ጫላ በንቲን በመተካት ቢጀምሩም በአጋማሹ ገና ከጅምሩ ነበር ግብ ያስተናገዱት። በ50ኛው ደቂቃ ብሩክ ማርቆስ ያሻማውን የማዕዘን ምት ግርማ በቀለ በግንባሩ በመግጨት ሀዲያን ዳግም ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛውን አጋማሽ ይበልጥ ጫና በመፍጠር የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ54ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ መነሻውን ባደረገ አጋጣሚ ፀጋዬ ብርሃኑ ፍፁም ያለቀለት አጋጣሚ ቢያገኝም መጠቀም ሳይችል የቀረበት እንዲሁም በ59ኛው ደቂቃ ደግሞ ስቲቨን ኒያርኮ በግሩም ሁኔታ ከሳጥን ውጭ ያደረገው እና በፍሬው ጌታሁን የዳነበት ኳስ መሪነታቸውን ለማሳደግ የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

በሂደት ድሬዳዋ ከተማዎች ሱራፌል ጌታቸው እና አድናን ዓሊን ተክተው በማስገባት የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ በተሻለ ታታሪነት በመጫወት ጫናዎችን ማሳደር የጀመሩ ቢሆንም ከማዕዘን ምቶች ከሚደረጉ ሙከራዎች በዘለለ በክፍት ጨዋታ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ተመልክተናል።

ደቂቃዎች መግፋትን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች በቁጥር በርክተው ጥቃቶችን ለመሰንዘር በሚሞክሩበት ወቅት በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት አራት ደቂቃዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ወጣቱ መለሰ ሚሻሞ ከባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ የደረሰውን ኳስ ከእያሱ ለገሰ ጋር ታግሎ ሀዲያ ሆሳዕናን ለ3-1 አሸናፊነት ያበቃችውን ኳስ አስቆጥሯል።

ጨዋታው በበላይነት ያጠናቀቁት የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በመስመሮች እንዳያጠቁ በመከልከል የሚገኙ ክፍተቶችን ለማጥቃት ጥረት አድርገን ውጤታማ ሆነናል ሲሉ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ ደግሞ ከዕረፍት በኋላ ባልጠበቁት ሰዓት በተፈጠረ ስህተት ግብ በማስተናገዳቸው ቡድናቸው ለመረጋጋት እንደተቸገረ ሲገልፁ በተጫዋቾቻቸው ላይ የሚታየው መዘናጋት እና አለመግባባቶችን ማረም እንደሚኖርባቸው ገልፀዋል።

ያጋሩ