ክፍት የነበረው የወልቂጤ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በመስፍን ታፈሰ ብቸኛ ጎል ቡናማዎቹን ባለድል አድርጓል።
በተመስገን በጅሮንድ አስደናቂ ጎል ባህር ዳር ከተማን ካሸነፈው ስብስባቸው ወልቂጤዎች ቴዎድሮስ መላኩ ፣ ሳሙኤል አስፈሪ ፣ ፋሲል አበባየሁ እና አቤል ነጋሽን በብርሀኑ ቦጋለ ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ አቡበከር ሳኒ እና ብዙአየሁ ሰይፉ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲገቡ ከሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ማግስት ቡናማዎቹ ከኋላ መስመራቸው ላይ ዘነበ ከድር እና ራምኬል ጀምስን በኩዋኩ ዱሃ እና ኃይለሚካኤል አደፍርስ በመለወጥ ለዛሬው ፍልሚያ ቀርበዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ የመሩት ይህ ጨዋታ በቡድኖቹ በኩል ሁለት መልክ የነበረው የመጀመርያ አጋማሽ እንቅስቃሴ ሲያስመለክቱን ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በ13ኛው ደቂቃ የጨዋታውን ልዩነት የቀየረች ድንቅ ጎል ማግኘት ችለዋል። በቅብብሎች ከአንበሉ አማኑኤል የተነሳውን አብዱልከሪም ወርቁ ተቀብሎ በጥሩ መንገድ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን መስፍን ታፈሰ በግሩም ሁኔታ ኳሱ ባልተለመደ ግራ እግሩ በመምታት ቡናን ቀዳሚ አድርጓል።
በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ጎል መገኘቱን ተከትሎ የጨዋታው እንቅስቃሴ የበለጠ በተጨማሪ ጎሎች ተጋግዞ ይቀጥላል ቢባልም እንደታሰበው ሳይሆን ጨዋታው ሊቀዘቅዝ ችሏል።
ወልቂጤዎች የመጀመርያው 15 ደቂቃ ከነበራቸው የመከላከል ባህሪ ወጥተው በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ አቻ ለመሆን የቡናን መከላከል ለማስከፈት ጥረት ለማድረግ ቢሞክሩም አደጋ መፍጠር ተቸግረዋል። ቡናማዎቹ ኳስን ተቆጣጥሮ ብልጫ ለመውሰድ ካሳዩት የጨዋታ መንገድ በመውጣት በረጃጅም ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞከሩም የተሳካ የጎል ዕድል የፈጠሩት በ30ኛው ደቂቃ በብሩክ በየነ ከመስመር የተሻገረትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር ቢመታውም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በቀላሉ ሲያድንበት ነበር። በድጋሚ መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ጫላ ተሺታ በግንባሩ ቢመታውም በድጋሚ ጀማል ጣሳው ያዳነው ከዕረፍት በፊት የቡናማዎቹ ሙከራዎች ነበሩ። ሰራተኞቹ ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ አቻ መሆን የሚችሉበትን ሁለት የጎል ሙከራዎችን በአጥቂያቸው ጌታነህ ከበደ አማካኝነት ማግኝት ችለው የነበሩ ቢሆንም የግቡን መረብ መድፈር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የቀጠለው ጨዋታ በመጀመርያው አምስት ደቂቃዎች ወልቂጤ በአጥቂያቸው ጌታነህ ከበደ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናዎች በአብዱልከሪም እና ብሩክ በየነ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ሙከራ በማድረግ ጨዋታውን ወደ ጥሩ ፉክክር ቀይረውታል።
የቡድኖቹ እንቅስቃሴ አንዴ ቀዝቀዝ አንዴ ሞቅ እያለ ቀጥሎ በ67ኛው ደቂቃ የቡናማዎቹ ነፃ የጎል አጋጣሚ አግኝተው ሮቤል ተክለሚካኤል ከጨዋታ ውጭ አቋቋም መስሎት ተዘናግቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል መልካም አጋጣሚ ነበር።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጠራ የጎል ሙከራ ሳንመለከት በጨዋታው ወደ መጠናቀቂያ ደርሶ በ89ኛው ደቂቃ የቡና ተከላካዮች ከሜዳ ክፍላቸው ኳሱን ማራቅ አቅቷቸው አፈወርቅ ኃይሉ አግኘቶ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል የመታውን ግብ ጠባቂው በረከት አማረ በጥሩ የማዳን አቅም ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ እንዳይጋራ አድርጓል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና አንድ ለምንም አሸነፊነት ተጠናቆ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ ሲያስችል በአንፃሩ ወልቂጤዎች ከሁለት ተከታታይ ድል በኋላ የመጀመርያ ሽንፈታቸውን እንዲያስተናግዱ ሆኗል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች ቡድናቸው በጫና ውስጥ ሆኖ የመጀመርያውን ድል ያሳኩት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በግላቸው ምንም ዓይነት ጫና ያልነበረባቸው መሆኑን እና በተጫዋቾች ላይ የተወሰነ ጫና እንደነበረ ገልፀው የአንበላቸው አማኑኤልን በፈለገው መንገድ እንዳይጫወት ወልቂጤዎች ያደረጉት ታክቲክ በሁለተኛ አጋማሽ ብልጫ እንደወሰዱባቸው ተናግረዋል። መጀመርያ ሽንፈታቸውን ያገኙት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው የተሸነፉበት መንገድ ያላስደሰታቸው ቢሆንም በመጀመርያው አጋማሽ ተጫዋቾቻው የጥንቃቄ አጨዋወት መምረጣቸው ውጤት ከመፈለግ አንፃር እንደሆነ ተናግረው በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ ገልፀዋል።