ሚኬል ሳማኬ ድንቅ በነበረበት የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ 2ኛ ዙር ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ፋሲል ከነማ በሴፋክሲያን 1-0 ተሸንፏል።
ዓምና ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ በማጠናቀቅ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበረው ፋሲል ከነማ ከቱኒዚያው ሴፋክሲያን ጋር ባህር ዳር ላይ ከነበረው የመጀመሪያ ጨዋታ ተከላካይ ክፍል ላይ አስቻለው ታመነን በመናፍ ዐወል በመተካት ብቻ ለመልሱ ግጥሚያ ወደ ሜዳ ገብቷል።
ጨዋታውን ከፍ ባለ ጫና የጀመሩት ሴፋክሲያኖች በተለይም በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ከባድ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በአንፃሩ በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ ያሳለፉት ፋሲሎች በሁለት አጋጣሚዎች ከቀኝ መስመር ለፍቃዱ ዓለሙ ካሻገሯቸው ኳሶች ብቻ ወደ ግብ መድረስ ችለው ነበር።
በአጋማሹ በድምሩ አምስት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን አድርገው ሁለት ጊዜ ደግሞ በግቡ ብረቶች ሙከራዎቻቸው የተመለሱባቸው ሴፋክሲያኖች 39ኛው ደቂቃ ላይ በለስ ቀንቷቸዋል። በፋሲል ሳጥን መግቢያ ላይ ሁሴን ዓሊ እና አብደላ አምሪ አንድ ሁለት በመቀባበል አምሪ ያሳለፈለትን ኢስማኤል ዲያኬይት በግራ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ግብ አድርጎታል።
ሴፋክሲያኖች ከጨዋታ ብልጫ ባሻገር በተከተሉት የኃይል አጨዋወት በአጋማሹ በአራት አጋጣሚዎች የፋሲል ተጫዋቾች የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ የሚያስገድዱ ጥፋቶችን መስራታቸውን ተከትሎ አፄዎቹ ዕረፍት መውጫው ላይ ስሜታዊ ሆነው ከአርቢትሮች ጋር የቃላት ልውውጥ ሲያደርጉ ተስተውሏል።
ከዕረፍት መልስ ፋሲል ከነማ የተሻለ መረጋጋት ሲታይበት በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ ወስዷል። ሆኖም 55ኛ ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ በግራ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ካደረገው ሙከራ ሌላ አደጋ መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ የመልሶ ማጥቃት ቁመና የታየባቸው ሴፋክሲያኖች ሚኬል ሳማኬ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ካራቃቸው ሁለት ኳሶች ውጪ በቀዳሚዎቹ 20 ደቂቃዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ጫናቸው ቀንሶ ታይቷል።
ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ ግን የጨዋታው መልክ እየተቀየረ የመጣ ሲሆን ሴፋክሲያኖች ደጋግመው ወደ ግብ የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ታይተዋል። በተለይም 77ኛው ደቂቃ ላይ ሀሽራፍ ሀቢቢሲ ያደረገው ለጎል የቀረበ ሙከራ ድንቅ ሆኖ በዋለው ሚኬል ሳማኬ ቅልጥፍና ግብ ከመሆን ድኗል። የቡድኑ ጫና እስከመጨረሻው ደቂቃ ቀጥሎ ወደ ፍፃሜው ሲቃረብ የቱኒዚያው ክለብ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ቢችልም ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ተሽሮበት ጨዋታው በ1-0 ውጤት ተፈፅሟል።
በዚህም የቡሩንዲው ቡማሙሩን በመርታት ለውድድሩ ሁለተኛ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ደርሶ የነበረው ፋሲል ከነማ በድምር ውጤት 1-0 ተሸንፎ የዘንድሮው የአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎውን አጠናቋል።