በዘንድሮ የሊጉ ውድድር የመጀመሪያው ተሰናባች አሠልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ሆኗል።
የ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በባህርዳር ከተማ እየተደረገ ሦስተኛ የጨዋታ ሳምንቱን ተሻግሯል፡፡ በሊጉ ተሳትፎን እያደረጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ ቡና እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ ብቻ ነጥብ በመጋራት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ከተቀመጠ በኋላ የክለቡ ቦርድ አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን ወደ ሀዋሳ እንደጠራ ዘገባ ሰርተን ነበር፡፡ ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት ሲመሩ ከነበረበት ኃላፊነት ክረምት ላይ ወደ ዋና አሰልጣኝነት መንበር እድገት አግኝተው የነበሩት ወንድማገኝ ክለቡ እያስመዘገበ ካለው ውጤት መነሻነት ገና በውላቸው መባቻ በይፋ ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች፡፡
የሲዳማ ቡና የቦርድ አመራሮች በትላንትናው ዕለት ከ8 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ከአሰልጣኙ እና ቡድን መሪው ጋር ንግግር ያደረጉ ሲሆን በስብሰባው የአሰልጣኙ ጥቅማጥቅም ተከብሮ ከክለቡ እንዲለያዩ ቦርዱ በመወሰኑ በይፋ መለያየታቸውን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ የቡድን መሪው አቶ አሸብርም እንዲነሱ ተደርጓል።
የክለቡ አመራሮች ከሁለቱ የስንብት ውሳኔ በዘለለ በሌሎች የክለቡ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ አካላትን ለማሰናበትም በሂደት ላይ መሆኑንም ጭምር ዝግጅት ክፍላችን ሰምታለች፡፡ ክለቡ አዲስ አሠልጣኝ እስኪሾም ድረስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ ጀምሮ በቀጣይ ባህር ዳር ላይ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በረዳት አሠልጣኙ ቾንቤ ገብረህይወት እንደሚመራ ተጠቁሟል።