ሁለት ክለቦች ላይ የገንዘብ ቅጣት ተጥሏል

በሦስተኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በተከሰቱ ግድፈቶች ዙሪያ ሊግ ካምፓኒው ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2015 የውድድር ዘመን እየተደረገ ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰ ሲሆን በጨዋታ ሳምንቱ በታዩ የዲሲፕሊን ጉድለቶች ዙሪያ የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ሥነ ስርዓት የዲሲፕሊን ኮሚቴ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የደረሱትን ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ በሁለት ክለቦች ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የመጀመሪያው ሲዳማ ቡና ቡና ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኛ ላይ አፀያፊ ስድብን ሰንዝረዋል በማለት ሊግ ካምፓኒው በክለቡ ላይ የ50 ሺህ ብር ቅጣት ጥሏል። በመቀጠል አርባምንጭ ከተማ መቻልን በረታበት ጨዋታ የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ የተመዘገበ የመለያ ቁጥሩ 1 ሲሆን 99 ለብሶ መግባቱን በመጥቀስ ቁጥር በመቀየሩ እንዲሁም ሊግ ካምፓኒው ከ1 እስከ 50 ቁጥር ብቻ ተጫዋቾች መጠቀም አለባቸው የሚለውን ህጉን በመጣሱ በሁለቱ ጥፋቶች ክለቡ በድምሩ የ6 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚቴው የአርባምንጭ ከተማ ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ቡድን መሪዎች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቡና የደጋፊ ማህበር ተወካይን ሊያነጋግራቸው የሚፈልግ በመሆኑ ጥሪ አቅርቦላቸዋል።