የታዋቂው ጋዜጠኛ ልጅ የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅሏል

አንድ ተጫዋች ከአሜሪካ ለሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው የዕድሜ እርከኑ ብሔራዊ ቡድን አባል ሆኗል።

ከሁለት ሳምንት በኋላ በሱዳን አዘጋጅነት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ውድድር ኢትዮጵያ በምድብ ለ ከዩጋንዳ እና ታንዛንያ ጋር መደልደሏ ይታወቃል።

ለዚህ ውድድር እንዲረዳ ለ48 ተጫዋቾች የመጀመርያ ጥሪ ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመርያ ዙር ምልመላውን በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት 28 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያ በዛሬው የቡድኑ ልምምድ በተገኘችበት አጋጣሚ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ሁሴን አብዱልቀኒ የመጀመርያ ልጅ አይመን ሁሴን ብሔራዊ ቡድኑን በመቀላቀል ልምምድ ሲሰራ ተመልክተናል።

አማካዩ አይመን ሁሴን የተወለደው አዲስ አበባ ሲሆን በአስራ አንድ ዓመቱ ወደ አሜሪካ በማቅናት በተለያዩ አካዳሚዎች ሥልጠና አግኝቶ አሳልፏል። በተለይ አሜሪካ በሚገኘው የስፔኑ ክለብ ቫላኒሺ አካዳሚ ቆይታ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቤልቪው ረሽ አካዳሚ የሚገኝ መሆኑን አውቀናል።

ያጋሩ