👉”ዋና አርዐያዬ ቤልጄማዊው አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ ነው”
👉”እዚህ ኢትዮጵያ ሀገሬ ቶጎ እንዳለው ነው ምቾት የሚሰማኝ”
👉”ቤት ስሆን የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን አያለው። ዘፈናቸው እና ዳንሳቸው ደስ ይለኛል”
👉”ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም ሊጉን የጀመረበት መንገድ ግልፅ ነው ፤ ዳግም ሻምፒዮን ለመሆን ነው”
👉”በዓመቱ መጨረሻ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ራሴን ማግኘት እፈልጋለው”
በዕለተ ማክሰኞ የካቲት 20 1996 በቶጎ ርዕሰ መዲና ሎሜ የተወለደው ግዙፉ አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በትውልድ ከተማው ሎሜ የእግርኳስ ባህል በጣም ስለነበር ገና ከጨቅላ እድሜው ጀምሮ ኳስን መጫወት እንደጀመረ ይናገራል። እስማኤል አሁን የሚኖርለት የእግርኳስ ፍቅር በአፍላነቱ ቢጀምረውም ቤተሰቡ በተለይ ደግሞ ወላጅ አባቱ በቀለም ትምህርቱ እንዲገፋ ስለሚፈልጉ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ዩኒቨርስቲ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ የነበረው የእግርኳስ ፍቅር ግን የአባቱን ቃል እንዲያሸንፍ አድርጎታል።
ሦስት ዓመት የሚወስደውን የዘመናዊ ታሪክ ጥናት (Contemporary History) ትምህርቱን ለመከታተል በሎሜ ዩኒቨርስቲ ገብቶ እየተማረ በሚያገኘው ትርፍ ጊዜ እግርኳስን እየተጫወተ ቢቆይም ለመመረቅ ወራት ሲቀሩት ግን የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ የልቡን ስሜት በማዳመጥ እግርኳስን የሙሉ ሰዓት ሥራው ለማድረግ ወሰነ። እርግጥ ይህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት የቀለም ትምህርቱን እየተማረ በሀገሩ አማተር እንዲሁም ነን ፕሮፌሽናል ሊግ ላይ ለሚሳተፉት ኦምኒ አጋዛ፣ ኤ ኤስ ኦ ቲ አር እና ሳራ ኤፍ ሲ ግልጋሎት ሲሰጥ ነበር። በትርፍ ጊዜው በሚጫወትበት ጊዜም ለብሔራዊ ቡድን መጠራቱ ትምህርቱን ትቶ ሙሉ ለሙሉ ወደ እግርኳስ እንዲያመዝን እንዳደረገው ይናገራል። ለኤ ኤስ ሲ ካራ ከተጫወተ በኋላም ዓምና ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅሏል።
1 ሜትር ከ82 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው እስማኤል በእግር ኳስ አርዐያ ያደረገውን ግለሰብ ሲናገር “ሲጀምር በሁሉም ጥሩ አጥቂዎች እማረካለው። ጨዋታዎችን ስመለከት አጥቂዎች ላይ ነው ትኩረቴን የማደርገው። ግብ ለማስቆጠር የሚያደርጉትን ነገር ለማየት እሞክራለው። ከሁሉም በላይ ግን ዋና አርዐያዬ ቤልጄማዊው አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ ነው። አካላዊ ሁኔታችንም ተመሳሳይ ነው። የእርሱን ጨዋታዎች ማየት በጣም ያሰደስተኛል።”
“የኢትዮጵያን ሊግ ለመልመድ ብዙም አልተቸገርኩም።” የሚለው እስማኤል ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ከዚህ ቀደም ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ በአጠቃላይ በሊጉ የተጫወቱ ቶጓዊያንን ስለ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠይቆ መረጃዎችን እንዳገኘ ነግሮናል። ተጫዋቹ ዓምና በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቶጎ ውጪ ባለሊግ የመጫወትን ፈተናን ቢጋፈጥም ራሱ እንዳለው ሊጉ እና ሀገሩ ሳይከብደው ለረጅም ሳምንታት የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃ ሲመራ ቆይቷል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገኙ ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ነገሮችን በቶሎ ተላምዶ ብቃቱን እንዲያሳይ እንደረዱት ይገልፃል። በተጨማሪም “ኢትዮጵያ በጣም ምርጥ ሀገር ነች። ህዝቡም በጣም ተወዳጅ እና ተንከባካቢ ነው። እዚህ ሀገሬ ቶጎ እንዳለው ነው ምቾት የሚሰማኝ።” በማለት ሀገሩ እንደተመቸው ሲናገር ይደመጣል።
እንዳለው ሊጉን ቶሎ ቢላመድም ግን ዓምና በግሉ የተፈራረቀ ስሜት እንዳሳለፈ አልሸሸገንም። “እንዳልኩት ሊጉን እና ሀገሩን በቶሎ በመልመድ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራው በጥሩ ብቃቴ ላይ በምገኝበት ሰዓት ጉዳት አጋጠመኝ። ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ለማግኘት ጠንካራ ትግል በሚያደርግበት ሰዓት እኔ በጉዳት ምክንያት እገዛ አላደረኩም ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ጉዳቴ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትም እንዳልዘልቅ አድርጎኛል። ይህ ቢያበሳጨኝም ክለቤ ግን መጨረሻ ላይ ሻምፒዮን በመሆኑ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል።”
እስማኤል ዓምና በአጠቃላይ በ18 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ያደረገው ሲሆን በአማካኝ በየ111.6 ደቂቃው ግቦችን በማስቆጠር አይምሬነቱን አሳይቷል። ዘንድሮ ደግሞ በአስገራሚ ሁኔታ በአማካይ በየ39.5 ደቂቃው ግቦችን በማስቆጠር የተጋጣሚ ተከላካዮችን ማራዱን ቀጥሏል። ተጫዋቹ የግራ እግሩን በዋናነት የሚጠቀም ቢሆንም ከስድስቱ ግቦች ሁለት ኳሶችን በቀኝ እግሩ ከመረብ አሳርፏል። ዓምና ደግሞ በግንባሩም ጭምር በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ምን አይነት የተሟላ አጥቂ እንደሆነ በሚገባ አሳይቷል። ይህንን የአጨራረስ ብቃት እንዴት እንዳዳበረው ስንጠይቀውም “ልምምድ ሜዳ ላይ በደንብ እሰራለው። በተለይ ጎል ፊት ብዙ ጊዜዬን አጠፋለው። ጨዋታ ላይም የሚታየው የልምምድ ስራ ውጤት ይመስለኛል። በአጠቃላይ ልምምድ ላይ በትኩረት ነው የምሰራው። ያም ነው ጨዋታ ላይ ስል እንድሆን የረዳኝ።” ብሎናል።
በ2020 ቻን ውድድር ላይ የሀገሩ ቶጎ መለያን ለብሶ ግልጋሎት የሰጠው እስማኤል ከዩጋንዳ ጋር በነበረው የምድቡ ሁለተኛ ፍልሚያ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠበትን ጊዜ የእስካሁኑ የእግርኳስ ህይወቱ ምርጡ አጋጣሚ አድርጎ እንደሚወስደው ከገለፀልን በኋላ በማስከተል ደግሞ ዓምና ለመጀመሪያ ጊዜ በክለብ ህይወቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ቻምፒዮን የሆነበትን ዓመት እንደማይረሳ አጫውቶናል።
የሁለት እህት እና ወንድም ታላቅ የሆነው እስማኤል ዘንድሮ በግሉ ማሳካት ስለሚፈልገው ነገር ይህንን ብሎናል። “ዋነኛው በግሌ ማሳካት የምፈልገው ነገር በዓመቱ መጨረሻ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ራሴን ማግኘት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በድጋሜ የሊጉ አሸናፊ እንዲሆን መርዳት ነው።”
ለናይጄሪያ ሙዚቃዎች ልዩ ፍቅር እንዳለው የሚናገው እስማኤል በተለይ ለጨዋታ ወደ ሜዳ ሲጓዝ በጆሮዎቹ የናይጄሪያዊውን ራፐር ኦላሚዴ ዜማዎች አዘውትሮ ይሰማል። ከሀገራችን ደግሞ ለኦሮምኛ ሙዚቃ ልዩ ቦታ እንደሚሰጥ በሳቅ በተሞላው ንግግሩ አጋርቶናል። “ቤት ስሆን የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን አያለው። ዘፈናቸው እና ዳንሳቸው ደስ ይለኛል። አሁን ግን የዲዲ ጋጋ እና ራሄል ጌቱ አድናቂ ነኝ። የእነርሱን ሙዚቃ ነው ብዙ ጊዜ የምከፍተው።”
በመጨረሻም “ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም ሊጉን የጀመረበት መንገድ ግልፅ ነው ፤ ዳግም ሻምፒዮን ለመሆን ነው። ኢንሻአላህ ዋንጫውን እንደምናነሳም እርግጠኞች ነን።” በማለት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታ አገባዷል።