አራተኛ የጨዋታ ሳምንት ነገ በሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል። እኛም ሁለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፋችን አቅርበናል።
አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሊጉ ካቆሙበት የቀጠሉትን ቅዱስ ጊዮርጊሶችን ከጨዋታ ጨዋታ የመሻሻል ምልክቶችን እያሳዩ ከሚገኙት አዳማ ከተማዎች ጋር የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
በተከታታይ በተለያየ መንገድ ጠንከር ካሉ ተጋጣሚዎች ጋር የተጫወቱት አዳማ ከተማዎች አምና በመከላከሉ ረገድ የነበራቸውን ጥንካሬ ይበልጥ እያጎለበቱት ያሉ ይመስላል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች እንደ ቡድን ከፍ ባለ ትጋት በመንቀሳቀስ ለተጋጣሚዎች ምቾት እየከለከለ የሚገኘው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግዱ መውጣታቸው በመልካምነት የሚነሳ ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ ግን ቡድኑ ቀሪ ስራዎች ቢጠብቁትም መጠነኛ መሻሻሎች ግን ስለመኖራቸው መናገር ይቻላል።
የአምና አሸናፊዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በግቦች የተንበሸበሸ አስደናቂ የሊግ አጀማመርን እያደረጉ ይገኛሉ። በመከላከሉ ረገድ እስካሁን ይህ ነው የሚባል ፈተና ያልቀመሰው ቡድኑ ከግቦች(13) ባለፈ በግብ ሙከራ(45) እንዲሁም ዒላማውን በጠበቀ ሙከራ(20) በሊጉ የሚስተካከላቸው አለመኖሩ የቡድኑ ማጥቃት እጅግ አስፈሪ ስለመሆኑ በሚገባ ያስረዳል።በሊጉ አናት የሚገኙት ፈረሰኞቹ በነገው ጨዋታ እስካሁን ከገጠሟቸው ተጋጣሚዎች በተሻለ በህብረት የሚንቀሳቀስ እና በአንፃራዊነት የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት ካለው አዳማ ጠንካራ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ይገመታል።
በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በፈረሰኞቹ በኩል የሚጠበቀው ተጫዋች ሲሆን በመከላከል ሆነ በማጥቃቱ እጅግ አስደናቂ ትጋት እያሳየ የሚገኘው ዳዋ ሆቴሳ ደግሞ በአዳማዎች በኩል ልዮነት ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች ነው። በነገው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ በሆነ ስብስብ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 40 ጊዜያት የተገኛኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀያ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ በአንፃሩ ሰባት ጊዜ ሲረታ አስራ ሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት የሳምንቱን የመክፈቻ ጨዋታ ሲመራ ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና አበራ አብርደው ረዳቶቹ እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ በአራተኛው ዳኝነት ለጨዋታው ተመድበዋል፡፡
ወልቂጤ ከተማ ከ ሃዋሳ ከተማ
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት ያስተናገዱትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የነገው የ10 ሰዓት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንደመስፈንጠሪያ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ጨዋታ እንደመሆኑ ትኩረትን ይስባል።
በርከት ያሉ ተጫዋቾችን እንደማዘዋወራቸው ሳይጠበቁ የተሻለ የውድድር ዘመን ጅማሮ ማድረግ ችለው የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ከኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት ለማገገም በነገው ጨዋታ በተሻለ ፍላጎት ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ቡድኑ መጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በተለይ በማጥቃቱ ረገድ የሚስተዋልበትን የቅንጅት ሂደት ግን መቅረፍ የግድ ይለዋል።
እንደ ወልቂጤ ሁሉ በማጥቃት ረገድ ከፍ ያለ የሀሳብ እጥረት የሚስተዋልባቸው ሀዋሳ ከተማዎች ገና ከወዲሁ በሁለት ጨዋታ ሽንፈት ማስተናገዳቸው በተወሰነ መልኩ ጫና ውስጥ እየከተታቸው ይገኛል። በመሆኑም ቡድኑ ከዚህ የተቀዛቀዘ ስሜት ለመውጣት ከነገው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብን ያልማሉ።
በሊጉ በአማካይ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ወልቂጤ ከተማ(14ኛ) እና ሃዋሳ ከተማ(16ኛ) ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ከተጋጣሚ ስህተቶች በሚነሱ ኳሶች ላይ የተንጠለጠለ ማጥቃት አማራጭን የሚጠቀሙት ቡድኖች በምን መልኩ ጨዋታውን ይቀርቡታል የሚለው ጉዳይ ትኩረትን የሚስብ ነው።
በነገው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማዎች ቅጣት ላይ የሰነበተውን ተከላካያቸው በረከት ሳሙኤልን ከቅጣት መልስ የሚያገኙ ሲሆን በነገው ጨዋታ የአማካያቸው አዲሱ አቱላ የመሰለፉ ነገር ግን አጠራጣሪ ሆኗል።በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች የነገውን ጨዋታ በሙሉ ስብስባቸው የሚከውኑ ይሆናል።
ለአራት ያክል ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በሁለቱ ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ የቀሩትን ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በመሸናነፍ የተካፈሏቸው ናቸው።
ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ የመሀል ዳኛ ሆኖ ለጨዋታው ሲመደብ ፣ ሙስጠፋ መኪ እና ወጋየሁ አየለ በረዳትነት እንዲሁም ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ለጨዋታው የተመደበው ዳኛ ነው።