ሪፖርት | አዝናኝ የነበረው ጨዋታ በኃይቆቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ሰባት ጎሎች ተስተናግደውበት ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን አሸናፊ በማድረግ ተገባዷል።

ከኢትዮጵያ ቡና የጠባብ ውጤት ሽንፈት በኋላ ወልቂጤዎች ጀማል ጣሰው፣ ብርሀኑ ቦጋለ፣ አዲስአለም ተስፋዬ፣ አፈወርቅ ኃይሉ፣ ተመስገን በጅሮንድ እና አቡበከር ሳኒን በሮበርት ኦዶንካራ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ ሳሙኤል አስፈሪ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ፣ አቤል ነጋሽ እና የኃላሸት ሰለሞን በመተካት ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ በአዳማ ከተማ የተሸነፉት ሀዋሳዎች ፀጋአብ ዮሐንስ፣ ላውረንስ ላርቴ፣ መድሃኔ ብርሀኔ እና አብዱልባሲጥ ከማልን በሰለሞን ወዴሳ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ አቤኔዘር ኦቴ እና በቃሉ ገነነን ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው ገና በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች እጅግ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር ጀምረዋል። በዚህ ደቂቃም የወልቂጤ ከተማዎች መዘናጋትን ተከትሎ በቃሉ ገነነ ኳሱን አግኘቶ ሳጥን ውስጥ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ሙጂብ ቃሲም አቀብሎት ሙጂብ በደካማ አጨራረስ ግብጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ አድኖበታል።

በፈጣን እንቅስቃሴ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስደው በመጫወት የዘለቁት ኃይቆቹ የመጀመርያ ጎላቸውን በ8ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ዓሊ ሱሌማን በጥሩ መንገድ ያቀበለውን ሙጂብ ቃሲም ወደ ጎል ሲመታው ግብጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ ኳሱን በሚገባ አለመቆጣጠሩን ተከትሎ ሲተፋው ኤፍሬም አሻሞ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ሠራተኞቹ ጥቃት ለመሰንዘር በረጃጅም ኳሶች ወደ ፊት ቢሄዱም በ13ኛው ደቂቃ የጌታነህ ከበደ የቅጣት ምት ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው የሚጠቀስ ሆኖ አልፏል። የወልቂጤዎቹን ያልተረጋጋ የመከላከልን እንቅስቃሴ ለመጠቀም ሲንቀሳቀሱ የታዮት ኃይቆቹ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሁለተኛ ጎላቸውን በ16ኛው ደቂቃ ማግኘት ችለዋል። ጎሉንም ዓሊ ሱሌማን በጥልቀት ሳጥን ውስጥ ኳሱን አግኘቶ በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን የግቡ ቋሚ ሲመልሰው ሙጂብ ቃሲም አግኝቶ የቡድኑን የጎል መጠን ከፍ አድርጎታል።

ወልቂጤዎች አንድም የጠራ የጎል ሙከራ ለማድረግ ቢቸገሩም ወደ ጨዋታው ሊመለሱበት የሚችሉበትን ጎል በ31ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ጎሉንም ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት ብዙዓየው ሰይፈ በአስደናቂ ሁኔታ አስገኝቶታል።

ክፍት እና ሳቢ የነበረው የሁለቱም ቡድኖች እንቅስቃሴ በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎሎች የሚቆጠሩበትን ፉክክት እንደሚኖረው ፍንጭ የሰጠ ነበር ። ሁለት የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥረው ሁለቱንም ወደ ጎልነት የቀየሩት ሀዋሳዎች እየተቀዛቀዙ ሲመጡ በአንፃሩ ሠራተኞቹ የአቻነት ጎል ፍለጋ ያሳዮት ታታሪነት ተሳክቶላቸው በ45ኛው ደቂቃ ወደ አቻነት የተሸጋገሩበትን ጎል አግኝተዋል። የሀዋሳዎች መከላከል ስህተት የፈጠረላቸውን ዕድል የኃላሸት ሰለሞን አግኝቶ ያቀበለውን ጌታነህ ከበደ በግራ እግሩ በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። አጋማሹም በሁለት አቻ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ ጎል ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በሁለቱም በኩል ቀጥሎ ታይቷል። የአሠልጣኝ ዘርዓይ ተጫዋቾች ጨዋታውን መምራት የሚችሉበትን ዕድል የሠራተኞቹ ተከላካይ ዋሁብ አዳምስ የሰራውን ስህተት ሙጂብ ቃሲብ አግኝቶ ለዓሊ ሱሌማን ቢያቀብለውም ግብጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ ያዳነበት አጋጣሚ ሲጠቀስ ብዙም ሳይቆይ በወልቂጤ በኩል በጌታነህ ከበደ አስደንጋጭ የቅጣት ምት ሙከራ ተስተናግዷል።

በጥሩ የማጥቃት ምልልስ የቀጠለው ጨዋታ ሀዋሳዎችን በድጋሚ ወደ መሪነት የቀየረች ጎል በ53ኛው ደቂቃ ተገኝታለች። ከሰለሞን ወዴሳ በረጅሙ ከሀዋሳ የሜዳ ክፍል የተላከውን ሙጂብ ቃሲም ፍጥነቱን እና ጉልበቱን ተጠቅሞ የወልቂጤን ተከላካይ በማለፍ በጥሩ አጨራረስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስገኝቷል።

በቡድናቸው ውስጥ ተከታታይ ሁለት ሽንፈት እና ሁለት አቻ ዋጋ እንደሌለው ከጨዋታው በፊት የተናገሩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራ ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት በድጋሚ ወደ ጨዋታው ለመግባት ጥረት በማድረግ ከማዕዘን ምት ተሻጋሪ ኳስ በዋሁብ አዳምስ የግባር ኳስ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት እንዲሁም በጌታነህ ከበደ የቅጣት ምት ኳስ ጥቃት ቢሰነዝሩም ሊሳካላቸው አልቻለም።

የተጫዋች ቅያሬያቸው ስኬታማ ያደረጋቸው አሰልጣኝ ዘራይ ሙሉ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን የገደሉበትን አራተኛ ጎል ማግኘት ችለዋል። በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር ዓሊ ሱሌማን ተነስቶ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ በአስደናቂ ሁኔታ ያሻገረለትን ሙጂብ ቃሲም በግንባሩ በመግጨት ጎል አስገኝቶ ሐት-ትሪክ ሰርቷል። ሙጂብ ቃሲም ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በመቀጠል ሐት-ትሪክ የሰራ ሁለተኛው ተጫዋችም ሆኗል።

ያላለቀው ጨዋታ ወደ መጨረሻው ደቂቃ ደርሶ ሠራተኞቹ የጎሉን መጠን የሚያጠቡበትን የጎል አጋጣሚ 88ኛው ደቂቃ በየኃላሸት ሰለሞን አማካኝ ቢፈጥሩ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ሆኖም በተጨማሪ ደቂቃ የሀዋሳ የሜዳ ክፍል ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዋሳ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወደ አሸነፊነት የተመለሱት የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘራይ ሙሉ ጨዋታው ለተመልካች አዝናኝ የነበረ ቢሆንም ለእሳቸው አስጨናቂ እንደነበረ በመግለፅ በዛሬው ጨዋታ በአጥቂ ክፍላችው መሻሻል ቢመለከቱም በተቃራኒው ከኃላ ክፍላቸው ከትኩረት ማጣት የሚሰሩ ስህተቶችን እንደሚያርሙ ተናግረዋል። ጨምረውም የሙጂብ ወደ ጎል አግቢነት መመለስ አቅደውበት የመጡበት እንደሆነ ተናግረዋል። ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አዝናኝ ጨዋታ እንደነበረ ጠቁመው ያልተፈለገ ጉዳት የገጠማቸው መሆኑ ውጤቱን እንደፈለጉት እንዳላገኙት እና በቀጣይ በሁሉም ክፍል መሻሻል እንዳለባቸው ሀሳባቸውን ገልፀዋል።