ሪፖርት | አዞዎቹ እና ነብሮቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ የነበረው የአርባምንጭ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ፍልሚያ ያለ ጎል ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ በመቻል ላይ ከተቀናጀው ድል የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርጓል፡፡ በዚህም የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን በተቀላቀለው አቡበከር ሻሚል ምትክ አንዱአለም አስናቀን በብቸኝነት ሲተካ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ተከታታይ ድላቸውን ተጎናፅፈው ለዛሬው ጨዋታ በቀረቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል መሳይ አያኖን ወደ ሀገሩ በግል ጉዳይ አምርቶ በተመለሰው ግብ ጠባቂው ፔፕ ሰይዱ ፣ ስቴፈን ኒያርኮን ከጉዳት በተመለሰው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ተክተዋል፡፡

07:00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው መሪነት በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አርባ አምስት ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴን ከመመልከት ባለፈ ብዙም የግብ ዕድሎችን ለማየት ያልታደልንበት ነበር፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች በተለመደው ረጃጅም እና ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች ከአጥቂ ጀርባ በመጣል ለመጫወት ፣ ሀድያ ሆሳዕናዎች በአንፃሩ በአንድ ሁለት ቅብብል በቀኝ መስመር ፀጋዬ ብርሀኑን እና ብርሃኑ በቀለን በሂደት ለመጠቀም ቢታትሩም ጨዋታው ከነበረው ደካማነት አኳያ የጠራ የግብ ዕድልን አልታየበትም፡፡ በጨዋታው የነበረችውን አንድ ሙከራ ለማየትም ሰላሳ ደቂቃዎች መጠበቅ ግድ ብሎናል፡፡

አማካዩ ቡጣቃ ሻመና ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ አክርሮ ሲመታ ሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ ፔፕ ሰይዶ ሳይቸገር የያዘበት ቀዳሚዋ እና ብቸኛዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች፡፡ በአጋማሹ ሀድያ ሆሳዕናዎች በተወሰነ መልኩ መቀዛቀዛቸውን ተከትሎ ካደረጓት ሙከራ በኋላ የተነቃቁ የሚመስሉት አርባምንጭ ከተማዎች ከመስመር ወደ ውስጥ በሚጣሉ ኳሶች አጋጣሚዎችን ለመፍጠር በቀሩት ደቂቃዎች ብልጫ መውሰድ ችለው ቢታዩም የመጨረሻዋን የኳሷን ማረፊያ ሊጠቀም የሚችል ሁነኛ ተጫዋች ባለ መኖሩ ደካማ ይዘትን የተላበሰው ቀዳሚው አጋማሽ ከነበረው ደብዛዛ ቅርፅ ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃራዊ መሻሻሎችን ያስተዋልንበት ሆኖ ማየት የቻልንበት መሆን ቢችልም ከጎል ሙከራዎች ግን የሳሳ ሁለተኛ አርባ አምስትን አይተንበታል፡፡ ነብሮቹ ኳስን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ ጥቃት ለመሰንዘር አዞዎቹ በተለምዷዊ የረጃጅም ኳስ አጠቃቀም ላይ ትኩረታቸውን አይተው ለመንቀሳቀስ ጥረዋል፡፡ 56ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ቡጣቃ ሻመና ከቀኝ የሀድያ የግብ ክልል ወደ ሳጥን ውስጥ ሲያሻግር ወርቅይታደስ አበበ ደርሶ ቢመታትም የሄኖክ አርፊጮ ጥረት ታግዞበት ለጥቂት ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ ግብ ለማግኘት የፈለጉ የሚመስሉት አርባምንጭ ከተማዎች ከ4-3-3 የጨዋታ አደራደር ወደ 3-4-3 አሸናፊ ኤልያስን በአህመድ ሁሴን ተክተው ወደ ሜዳ አስገብተዋል፡፡

70ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን ከቡጣቃ ሻመና የተቀበለውን ኳስ ከተከላካዩ ዳግም በቀለ ጋር ታግሎ በማለፍ ወደ ጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው ፔፕ ሰይዶ በጥሩ ቅልጥፍ አውጥቶበታል፡፡ ስቴፈን ኒያርኮን ጉዳት በገጠመው ግርማ በቀለ ከለወጡ በኋላ መሀል ሜዳ ላይ መረጋጋት የታየባቸው ሀድያ ሆሳዕናዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸውን በጨዋታው አድርገዋል፡፡ ከተቋረጠ የቅብብል ሂደት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እግር የደረሰችዋን ኳስ አማካዩ ወደ ሳጥን ገፋ አድርጎ አክርሮ ሲመታ አቤል ማሞ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ ጨዋታው ከነበረው ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች አንፃር ኳስን ከመረብ ጋር ተዋህደው ሳንመለከት 0-0 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጠንካራ ቡድን እንዳላቸው ጠቁመው በጥንቃቄ ተጫውተው ጎል ለማስቆጠር እንደጣሩ ገልፀው የተሻለ ዕድል ፈጥረው የተገኙትን አለመጠቀም ላይ ክፍተት እንደነበረባቸው ተናግረዋል፡፡ የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ጠንካራ ተፎካካሪ እንደገጠማቸው ከተናገሩ በኋላ በሁለት ቀን ልዩነት መጫወታቸው ለድካም እንደዳረጋቸው እና ተጋጣሚያቸውም የመከላከል ኳሊቲ ያለው በመሆኑ አቻ ውጤቱ እንደሚገባቸው በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡