የኃይል አጨዋወት የበዛበት የባህር ዳር ከተማ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ከፍ ባለ ፉክክር ታጅቦ 1-1 ተጠናቋል።
በሁለተኛ ሳምንት በወልቂጤ ከተማ ከተረቱ በኋላ በሦስተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ሳያደርጉ የመጡት ባህር ዳር ከተማዎች ዳዊት ወርቁ ፣ ተስፋዬ ታምራት ፣ አለለኝ አዘነ ፣ የአብስራ ተስፋዬ ፣ ፍፁም ጥላሁን እና ኦሲ ማውሊን በያሬድ ባዬ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ፉአድ ፈረጃ ፣ በረከት ጥጋቡ ፣ ሐብታሙ ታደሰ እና አደም አባስ በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል። በሦስተኛ ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና የተረቱት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በመሐመድ አብዱለጢፍ ምትክ ብሩክ ቃልቦሬን ብቻ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ አካተው ገብተዋል።
ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች ላይ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው ሜዳ የገቡት ባህር ዳሮች ተጭነው መጫወት ችለዋል። ሆኖም በ7ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል ከሳተው ኳስ ውጪ ቡድኑ በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ግልፅ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ተቸግሮ ነበር። በሂደት ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት ብርትካናማዎቹ በመልሶ ማጥቃት ያልታሰቡ ጥቃቶችን በመሰንዘር የባህር ዳርን ጫና ለመግታት ችለዋል። በዚህ ሂደት የቀጠሉት ድሬዳዋዎች የመጀመርያ ጎላቸውን በ26ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ቢንያም ጌታቸው የተጣለለትን ኳስ ይዞ ወደ ፊት እየሄደ ባለበት ወቅት በያሬድ ባዬ ጥፋት በመሰራቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ያሬድ ታደሰ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
ባህር ዳሮች ጎል ቢያስተናግዱም በጥሩ ቅብብሎች ወደ ፊት በመሄድ ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም ከጨዋታ ውጭ አቋቋም እንቅስቃሴን ባለመቆጣጠራቸው ምክንያት ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ዕድሎች በቀላሉ ሲያመክኑ ተስተውሏል። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በራስ መተማመናቸው የጨመረው ድሬዳዋዎች በመልሶ ማጥቃት የባህር ዳርን መከላከል እየረበሹ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሄዷል። ሆኖም ጨዋተው በጥሩ ግለት እያመራ ባለበት ሰዓት በ36ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ሌላ መንፈስ የሚቀይር ድርጊት ሜዳ ውስጥ ተከስቷል። እንየው ካሳሁን አደም አባስ ላይ ከበድ ያለ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ በተጫዋቾች መካከል አለመግባባት ከመፈጠሩም ባሻገር አንድ ደጋፊ ወደ ሜዳ ዘሎ በመግባት የጨዋታውን ሂደት ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲያመራ አድርጎታል። ጨዋታውም ለደቂቃዎች ለመቋረጥ ከተገደደ በኋላ እንዲጀምር ሆኗል።
እንዳጀማመራቸው ያልሆኑን የጣና ሞገዶቹ ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ፉአድ ፈረጃ የጣና ቡድኑን አቻ የምታደርግ የቅጣት ምት ኳስ ግኝቶ በቀጥታ የመታውን ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ያዳነበት አደገኛ ሙከራ ነበር።
በአንድ ጎል ልዩነት እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ባህር ዳሮች በሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታው ጎል ለማግኘት ጥለውት የሚሄዱትን ክፍት ሜደ ድሬዳዋዎች ለመጠቀም ማሰባቸው ፈተና ቢሆንባቸውም 55ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጎልነት መቀየር የሚቻል አጋጣሚን አምክነዋል። ያሬድ ባዬ የተገኘውን ቅጣት ምት ፈጥኖ በማስጀመር ዱሬሳ ሹቢሳ ግብ ጠባቂውን ፍሬውን አልፎ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ጋናዊው ተከላካይ አሳንቴ ጎድፍሬድ ያዳነበት ለባህር ዳር አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
በሙሉ አቅማቸው ፋታ ሳይሰጡ ወደ ማጥቃቱ የገቡት የጣና ሞገዶቹ 60ኛው ደቂቃ እንየው ካሳሁን ዱሬሳ ሹቢሳ ላይ ጥፋት በመስራቱ በሁለት ቢጫ ማስጠንቀቂያ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ የበለጠ አቅም ፈጥሮላቸዋል። ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ባህር ዳሮች 64ኛው ደቂቃ ቻርልስ ሪባኑ ለጎል የቀረበ ሙከራ በቀኝ ጠርዝ መሬት ለመሬት የመታው እና ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ያዳነበት መልካም የጎል አጋጣሚ ነበር። በአንፃሩ ብርትካናማዎቹ በቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ባመዛኙ መከላከል ላይ ተጠምደው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል።
ሆኖም ግን የባህር ዳር ከተማን የጥቃት የበላይነት ቀጥሎ 74ኛው ደቂቃ ሳይታሰብ ፉአድ ፈረጃ ከሳጥን ውጪ በጥሩ ሁኔታ የመታውን ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በጥሩ ሁኔታ ቢያድንበትም ከሦስት ደቂቃ በኋላ የአቻነት ጎል ባህር ዳሮች አግኝተዋል። ከያሬድ ባዬ የተነሳውን ኳስ በረከት ጥጋቡ በጥሩ ዕይታ ያሳለፈለትን ዱሬሳ ሹቢሳ ጎል አስቆጥሮ የቡድኑን ደጋፊዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሲያነቃቃ ተስተውሏል።
የቁጥር ብልጫ እንደመውሰዳቸው እና ጎል ኳስቆጠሩ በኋላ ቀሪ ደቂቃዎች መኖራቸውን ተከትሎ ባህር ዳሮች ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር ከጨዋታው አንድ ነገር ይዘው ይወጣሉ ቢባልም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የወረደ መሆኑ ለድሬዳዋዎች እፎይታ ሰጥቶ ጨዋታው በተለያዩ ምክንያቶች ሲቆራረጥ ቀጥሎ በስተመጨረሻም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ማግኘት ይገባቸው እንደነበረ ተናግረው በተረጋጋ ሁኔታ ወደ ፊት አለመሄድ እና በአዕምሮ ዝግጁ አለመሆን አቻ ለመውጣት መገደዳቸውን ገልፀዋል። አክለውም የደጋፊው ጫና ቢኖርም ከዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ እንደነበረባቸው አያይዘው ተናግረዋል። የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በበኩላቸው በመጀመርያው አጋማሽ ቡድናቸው ብልጫ መውሰዱን ገልፀው ከዕረፍት በኋላ የነበረው ጨዋታ ሁኔታ ጥሩ እንዳልነበር ተናግረው ይህ ጨዋታ ነገ አራት ሰዓት ቢደገም ይህንን ቡድን አሸንፈውት እንደሚወጡ እና ቀይ ካርዱ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ጠቁመው በመቀጠልም የአቻው ውጤት እንደማይገባቸው ተናግረዋል።