“እውነት ለመናገር ከተፈለገ ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ደግመን ብንጫወት ይሄን ቡድን አሸንፈዋለው” አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ

ዓይን የሚስብ የሜዳ ላይ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታ በበርካታ የሜዳ ላይ ፍልሚያዎች ታጅቦ በአነጋጋሪ የአሰልጣኝ አስተያየት ተቋጭቷል።

የ4ኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ከቀትር በኋላ ያስተናገደው የባህር ዳር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በክስተቶች የተሞላ ነበር። በመቀመጫ ከተማው ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ የዕለቱ ተጋጣሚ በመሆኑ በስታዲየሙ ውስጥ የነበረው የደጋፊ ድባብ አንዱ ለግጥሚያው የተለየ ድባብ የፈጠረ አጋጣሚ ሲሆን ሜዳ ላይ የተፈጠሩ አወዛጋቢ ክስተቶች ደግሞ ይበልጥ ጨዋታው ውጥረት እንዲኖርበት አድርገዋል።

የመጀመሪያው ድሬዳዋ ከተማ በያሬድ ታደሰ ፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1-0 እየመራ ጨዋታው 36ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ እንየው ካሳሁን የጣና ሞገዶቹ የመስመር ተጫዋች አደም አባስ ተቀይሮ በመውጣት ለተጨማሪ ዕርዳታ ወደ ሆስፒታል እንዲያመራ ያስገደደ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተፈጠረው እሰጥ አገባ ነበር። ሜዳ ላይ ባሉ እና በተጠባባቂ ተጫዋቾች መሀል የታየው ይህ ሁኔታ ወደ ደጋፊውም ተዛምቶ አንድ ደጋፊ ወደ ሜዳ በመግባት ግርግሩን ሲቀላቀል የታየ ሲሆን አጋጣሚው ከቃላት ልውውጥ ሳያልፍ በግልግል በርዶ ጨዋታው ቀጥሏል።

ከዚህ በኋላም የጨዋታው ጠባብ የውጤት ልዩነት የፈጠረው የፍልሚያ ግለት የፌደራል ዳኛ ባህሩ ተካን ፊሽካ ደጋግሞ የሚያሰሙ ጉሽሚያዎች በርክተውበት የቀጠለ ሆኗል። በሜዳው የተለያዩ ክፍሎች የተመለከትናቸው እነዚህ በእንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ግጭቶች እየታዩ በመጨረሻም የቀይ ካርድ እንዲመዘዝ የግድ ሆኗል። በዚህም 60ኛው ደቂቃ ላይ የትኩረት ማዕከል ሆኖ የቀጠለው የብርቱካናማዎቹ የመስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን ዱሬሳ ሹቢሳ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተገዷል። በቀሪ ደቂቃዎች የባህር ዳሮችን ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት የተደረገ ትግል እና የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች አፀፋዊ ውጤት አሳልፎ ያለመስጠት ተጋድሎ ጨዋታው ለዓይን ማራኪ ሆኖ በ1-1 ውጤት እንዲጠናቀቅ ያደረገ ሆኗል።

የጨዋታው መነጋገሪያ ነጥቦች ግን ከ90 ደቂቃውም አልፈው አሰልጣኞች ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር በሚያደርጉት ቆይታ ላይም ተደግመዋል። ሜዳ ላይ በተሰጡት ውሳኔዎች እና በውጤቱ ደስተኛ ያልሆኑት የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

“አርባ አምስቱን ጥሩ ነበርን፡፡ ጥሩ የመንቀሳቀስ ከሌላው ጊዜ የተሻልን ነበርን፡፡ ከዕረፍት በኋላ ያለውን ነገር እንኳን ብዙም ባላወራው ደስ ይለኛል። እግርኳስ ተግባር ነው የሚፈልገው ፤ ህዝብ ያየናል በተግባር ነው፡፡ አቅም ያለው ሰው ያሸንፋል፡፡ ማንም እኔ ድጋፍ እንዲያደርግልኝ አልፈልግም እውነት ለመናገር ከተፈለገ ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ደግመን ብንጫወት ይሄን ቡድን አሸንፈዋለው፡፡ ግን በዳኝነት ምንም ዓይነት ሰበብ አላደረግም፡፡ ዳኞቹን የሚመለከት የራሳቸው አካል አለ። ግን እግርኳሱ ተግባር ነው ፤ አቅም ያለው ያሸንፋል፡፡ የኔ ቡድን ነገም ከነገ ወዲያም ማንንም ማሸነፍ ይችላል፡፡ ነገ ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ብንጫወት ይሄን ቡድን አሸንፈዋለው፡፡ ግን ለባህር ዳር ህዝብ ለክለቡም ለደጋፊውም ክብር አለኝ፡፡”

የጨዋታው የትኩረት ነጥብ በነበረው እንየው ካሳሁን የቀይ ካርድ ዙሪያ አሰልጣኙ በሰጡት አስተያየት ደግሞ “በእያንዳንዱ ነገር ተጫዋች ያጠፋል በቀይም ይወጣል ችግር የለውም፡፡ እንየው ጥፋተኛ ሊሆን ይችላል ፤ ዳኛው ወሰነ አለቀ። ግን እውነት በትክክል ዳኝቷል ? እርሱን ለዳኞች ትተናል፡፡” ብለዋል።

በመጨረሻም ውጤቱን ይዞ ለመውጣት እና ሁለተኛ ጎል ለማከል ቡድናቸው የተሻለ መረጋጋትን መላበስ እንደነበረበት ጠቁመው በመጨረሻ በውጤቱ ተገቢነት ዙሪያ “ለእኛ ተገቢ አይደለም። በደንብ አሸንፈን መውጣት እንችል ነበር ፤ ግን ሆኗል ቀጣዩንም እንጠብቃለን፡፡” በማለት የነበራቸውን ቆይታ ቋጭተዋል።