ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል አሳክቷል

በአራተኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በምክትል አሰልጣኞች መካከል የተደረገው የሁለቱ ቡናዎች ጨዋታ መስፍን ታፈሰ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን በወልቂጤ ከተማ ላይ ሲያስመዘግብ ከተጠቀመበት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አማኑኤል ዮሐንስን በሄኖክ ድልቢ ብቻ ሲለውጡ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ አስከፊ ሽንፈት አስተናግደው ለዛሬው ጨዋታ በቀረቡት ሲዳማ ቡናዎች በኩል ደግሞ ሰለሞን ሀብቴን በመሀሪ መና ፣ ሙሉቀን አዲሱን በቡልቻ ሹራ ተክተው ተጠቅመዋል፡፡

ጨዋታው ከጅምሩ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ኳስን ለመቆጣጠር የሚያስችል መልክ የነበረውን የአጨዋወት ይዘት መመልከት የጀመርነው በጊዜ ነበር፡፡ በቀኝ መስመር በኩል ወደ ተሰለፈው ጫላ ተሺታ በደንብ ተስበው በመጫወት የማጥቂያ መንገዳቸውን የመጠቀም እሳቤን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጫላ አማካኝነት ከመስመር ወደ ሳጥን በሚላኩ ኳሶች እና መሀል ክፍሉ ላይ የአብዱልከሪም ወርቁን የፈጠራ አቅም ተጠቅሞ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሙከራን ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ለዚህም ማሳያ 7ኛው ደቂቃ ጫላ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ሲያሻግር ኳሷ አቅጣጫ በመቀይሯ ግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ እንደምንም የያዘበት አጋጣሚ ቀዳሚዋ የጨዋታው ሙከራ ሆናለች፡፡ በእንቅስቃሴ ረገድ ሜዳ ላይ የማያስከፋ ፍሰትን ያደርጉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ኳስን በሚቀባበሉበት ወቅት በተደጋጋሚ በተጋጣሚያቸው ይነጠቁ ስለነበር የጨዋታ ሂደታቸውን ወደ መስመር አድርገው በሚሻገሩ ኳሶች አቀራረባቸውን አድርገው ተስተውሏል፡፡

መሀል ለመሀል ለአጥቂዎች በሚያልፉ እንዲሁም በመስመር በተለየ መልኩ ጫላ ተሺታን ዋነኛ ትኩረታቸው ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተሳክቶላቸው መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ ከአስራት ቱንጆ መነሻዋን ያደረገች ኳስ አብዱልከሪም ወርቁ እግር ስር ደርሳ አማካዩ የሲዳማ ቡናን የመሀል ተከላካይ ዝንጉነት ተጠቅሞ ያሾለከለትን ኳስ መስፍን ታፈሰ ወደ ጎልነት ለውጧት የመዲናይቱን ክለብ ቀዳሚ አድርጓል፡፡አድርጓል፡፡

ጎል ካስተናገዱ በኋላ በነፃነት ወደ ፊት ተስበው አቻ ለመሆን መንቀሳቀስ የቻሉት ሲዳማዎች በአማኑኤል እንዳለ የርቀት ሙከራ አድርገው ብረት መልሶባቸዋል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል በመሄዱ ረገድ ባይቸገሩም የኋላ መስመራቸው የአደራደር ስህተት ወጥ ካለመሆኑ አንፃር ሲፈተኑ አስተውለናል፡፡ ይሁን እንጂ 41ኛው ደቂቃ ላይ ከአማኑኤል እንዳለ የቀኝ መስመር የተነሳችን ኳስ በተከላካዮች በግንባር ስትገጭ ፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሲመታ በረከት አማረ እና የግቡ የላይኛው ብረት ተባብረው ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን በመቆጣጠር ለመጫወት ሙሉ ትኩረታቸውን አድርገው የተመለከትን ቢሆንም ሲዳማ ቡናዎች የኮሪደር አጨዋወት ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ተከትሎ በተደጋጋሚ ከሚጥሏቸው ተሻጋሪ ኳሶች አንፃር በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫን ማሳየት ችለዋል፡፡ በተለይ ሲዳማ ቡናዎች አቤል እንዳለን በአበባየው ዮሐንስ ፣ እንዳለ ከበደን በፀጋዬ አበራ ከተኩ በኋላ የመሀል ሜዳው ላይ ይበልጥ ንቃቶችን መስተዋል ጀምሯል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ከመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ አንፃራዊ መቀዛቀዞች ቢታይባቸውም ኳስን በሚያገኙበት ወቅት ግን በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ከመፍጠር አልዳዱም፡፡ ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን በመጣል አቻ ለመሆን በብርታት ይታትሩ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ሆነው መታየት ቢችሉም የሚሻገሩ ኳሶቻቸው የሚጠቀም ሁነኛ ተጫዋች አለመኖሩን ተከትሎ በብልጠን ግቡን ሲጠብቅ ለነበረው በረከት አማረ ሲሳዮች ሲሆኑ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ 68ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ አበራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ በረከት አማረ የመለሰበት የሁለተኛው አርባ አምስት የምትጠቀሰዋ ሙከራ ነበረች፡፡

ግብ ለማስቆጠር እጅጉን በተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ ላይ ይገኙ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በሌላ ሙከራቸው 79ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ የግብ ሙከራን አድርገዋል፡፡ መሀሪ መና ከማዕዘን ሲያሻማ ይገዙ ቦጋለ ጋር ደርሳ አጥቂው ወደ ጎል መትቶ በድጋሚ ስትመለስ ተከላካዩ ያኩቡ አግኝቷት ሲዳማን አቻ አደረገ ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ላይ ወጥታበታለች፡፡ ፍፁም ብልጫ እንደተወሰደባቸው የተረዱ የሚመስሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች አማካዩ አብዱልከሪም ወርቁን አስወጥተው በምትኩ ተከላካዩ ራምኬል ጀምስን ወደ ሜዳ በማስገባት ብርቱ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ተከትሎ 1-0 በማሸነፍ ሙሉ ሶስት ነጥብን ወደ ካዝናቸው ከተዋል፡፡

ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሀዘን ምክንያት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና አለመኖሩን ተከትሎ ቡድኑን መምራት የቻለው ምክትሉ ነፃነት ክብሬ ከውጤት አንፃር ያገኙት ነጥብ ጥሩ መሆኑን ጠቅሶ ከእንቅስቃሴ አንፃር ግን መጥፎ እንደነበሩ ጠቁመው ለዋንጫ ለሚጫወት ቡድን ግን ዋናው ሦስት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በምክትል አሰልጣኝ የተመራው ሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ቾንቤ ገብረህይወት በመጀመሪያው አጋማሽ አለመረጋጋቶች እንደነበሩ ጠቁመው በሁለተኛው አጋማሽ መረጋጋት ችለው የነበረ ቢሆንም ወደ ጎል በመቀየሩ ረገድ ግን ክፍተት እንነበረባቸው እንዲሁም ከባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንፃር ቡድኑ የተረጋጋ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡