ሪፖርት | መቻል ወሳኝ ድል አሳክቷል

መቻል ፋሲልን በመርታት የዓመቱ ሁለተኛ ሙሉ ነጥቡን አግኝቷል፡፡

በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ገጥሟቸው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት መቻሎች በሶስት ተጫዋቾች ላይ ሁለት ለውጥ አድርገዋል፡፡ ተክለማርያም ሻንቆን በዳግም ተፈራ ፣ ዳዊት ማሞን በግሩም ሀጎስ ፣ በረከት ደስታን በአንፃሩ በተሾመ በላቸው ተክተዋል፡፡ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ምክንያት የመጀመሪያውን ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር ካደረገ በኋላ በሊጉ ተጨማሪ ጨዋታዎችን ማድረግ ያልቻለው ፋሲል ከነማ የዛሬው መርሀግብርም ሁለተኛ ጨዋታው ነው፡፡

መከላከያ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ እየጣለ ከመምጣቱ አንፃር በጥብቅ መከላከል ወደ ሜዳ በገባበት እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በጣረበት እንዲሁም ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው አማካዮቻቸው ሱራፌል ዳኛቸው ፣ በዛብህ መለዩ እና ሽመክት ጉግሳ ካለመኖራቸው አንፃር ከተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎችን ለማግኘት ጥረት ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ተመልክተናል፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ለመሀል የተሰነጠቀለትን ኳስ ፈጣኑ የመቻል የመስመር አጥቂ ፍፁም አለሙ አግኝቷት ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ያስጣለበት መንገድ ቀዳሚዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች፡፡ ሶስት የጠሩ ሙከራዎችን ብቻ ባየንበት አጋማሽ 23ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ሁለተኛ ሙከራን አስተውለናል፡፡

በዚህም ደቂቃ ከቀኝ የመቻል የግብ አቅጣጫ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ መመልከት የቻልነው አለምብርሃን ይግዛው ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ምንተስኖት አዳነ ኳሷን ለማውጣት ሲሞክር በቅርበት ሳጥኑ ጠርዝ የነበረው ታፈሰ ሰለሞን አግኝቷት በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በድንቅ ብቃት አድኖበታል፡፡ ሶስተኛዋ ሙከራ ከቅጣት ምት 32ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች ያገኙትን አጋጣሚ ሳሙኤል ሳሊሶ በቀጥታ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ሳማኪ እንደምንም አውጥቷል፡፡

እንደ አጀማመራቸው ወደ ዕረፍት መባቻ ገዳማ መቀዛቀዝ የታየባቸው አፄዎቹ በማጥቃት ሻል ባሉት መቻሎች ጫና ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ወንድማገኝ ማርቆስን በአቤል እያዩ ለውጠው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በሁለቱም ቡድኖች የኳስ ቁጥጥሮችን መመልከት የቻልን ቢሆን ጥንቃቄ አዘል ጨዋታውን የመረጠ የሚመስለው እና ግብ ለማስቆጠር ገና በጊዜ ጥረት የጀመሩት መቻሎች ተሾመ በላቸው እና ምንይሉ ወንድሙን በእስራኤል እሸቱ እና በረከት ደስታ ከተኩ በኋላ እጅጉን ተሻሽለው መታየት ችለዋል፡፡

ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ 51ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አጥቂው እስራኤል እሸቱ ከቀኝ በኩል የተቀበለውን ኳስ ሁለት ጊዜ ብቻ ገፋ አድርጎ ከሳጥን ውጪ አስገራሚ ጎል በማስቆጠር ክለቡን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ለውጠው የኳስ ቁጥጥሩን በመውሰድ ጎል ለማስቆጠር ሲጥሩ አፄዎቹ ቢታዩም የመቻልን የጥብቅ መከላከል ፈተና መጋፈጥ ሳይቸሉ ጨዋታው 1ለ0 በጦረኞቹ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፋሲሉ አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ ጨዋታው የጥንቃቄ እንደሚሆን እንደገመቱ ያሰቡት እንደገጠማቸው ከተናገሩ በኋላ ጨዋታው ከባድ እንነበር ገልፀው በጉዳት የሌሉ ተጫዋቾች አለመኖራቸው እንደጎዳቸው የፊት መስመሩ በመሳሳቱ ተጋጣሚያቸው ያገኘውኝ ዕድል ተጠቅሞ እንዳሸነፋቸው ተናግረዋል፡፡ ድል የቀናቸው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በተከታታይ ቡድናቸው ከጣለው ነጥብ አንፃር የስነ ልቦና ችግር ቡድኑ ላይ መኖሩን ጠቁመው ይሄን ለማሻሻል ሶስት ነጥብ ማግኘታቸው ለዚህም ትልቅ ተጋድሎ ተጫዋቾቻቸው አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምስጋናን አበርክተዋል፡፡