መቻል ፋሲልን በእስራኤል እሸቱ ብቸኛ ጎል በመርታት የዓመቱን ሁለተኛ ሙሉ ነጥቡን አግኝቷል፡፡
በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ገጥሟቸው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት መቻሎች በሦስት ተጫዋቾች ላይ ሁለት ለውጥ አድርገዋል፡፡ ተክለማርያም ሻንቆን በዳግም ተፈራ ፣ ዳዊት ማሞን በግሩም ሀጎስ ፣ በረከት ደስታን በአንፃሩ በተሾመ በላቸው ተክተዋል፡፡ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ምክንያት የመጀመሪያውን ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር ካደረገ በኋላ በሊጉ ተጨማሪ ጨዋታዎችን ማድረግ ያልቻለው ፋሲል ከነማ የዛሬው መርሐግብርም ሁለተኛ ጨዋታው ነበር፡፡
መከላከያ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ እየጣለ ከመምጣቱ አንፃር በጥብቅ መከላከል ወደ ሜዳ በገባበት እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በጣረበት እንዲሁም ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው አማካዮቻቸው ሱራፌል ዳኛቸው ፣ በዛብህ መለዩ እና ሽመክት ጉግሳ ካለመኖራቸው አንፃር ከተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎችን ለማግኘት ጥረት ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ተመልክተናል፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ለመሀል የተሰነጠቀለትን ኳስ ፈጣኑ የመቻል የመስመር አጥቂ ፍፁም ዓለሙ አግኝቷት ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ያስጣለበት መንገድ ቀዳሚዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች፡፡
ሦስት የጠሩ ሙከራዎችን ብቻ ባየንበት አጋማሽ
23ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ሁለተኛ ሙከራን አስተውለናል፡፡ በዚህም ደቂቃ ከቀኝ የመቻል የግብ አቅጣጫ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ መመልከት የቻልነው ዓለምብርሃን ይግዛው ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ምንተስኖት አዳነ ኳሷን ለማውጣት ሲሞክር በቅርበት ሳጥኑ ጠርዝ የነበረው ታፈሰ ሰለሞን አግኝቷት በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በድንቅ ብቃት አድኖበታል፡፡ ሦስተኛዋ ሙከራ ከቅጣት ምት 32ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች ያገኙትን አጋጣሚ ሳሙኤል ሳሊሶ በቀጥታ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ሳማኪ እንደምንም አውጥቷል፡፡ እንደ አጀማመራቸው ወደ ዕረፍት መባቻ ገዳማ መቀዛቀዝ የታየባቸው አፄዎቹ በማጥቃት ሻል ባሉት መቻሎች ጫና ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ወንድማገኝ ማርቆስን በአቤል እያዩ ለውጠው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በሁለቱም ቡድኖች የኳስ ቁጥጥሮችን መመልከት የቻልን ሲሆን ጥንቃቄ አዘል ጨዋታውን የመረጠ የሚመስለው እና ግብ ለማስቆጠር ገና በጊዜ ጥረት የጀመሩት መቻሎች ጉዳት የገጠመው ተሾመ በላቸው እና ምንይሉ ወንድሙን በእስራኤል እሸቱ እና በረከት ደስታ ከተኩ በኋላ እጅጉን ተሻሽለው መታየት ችለዋል፡፡ ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ 51ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አጥቂው እስራኤል እሸቱ ከቀኝ በኩል የተቀበለውን ኳስ ሁለት ጊዜ ብቻ ገፋ አድርጎ ከሳጥን መትቶ በማስቆጠር ክለቡን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ከጎሉ መቆጠር በኋላ አፄዎቹ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ለውጠው የኳስ ቁጥጥሩን በመውሰድ ጎል ለማስቆጠር ሲጥሩ ቢታዩም የመቻልን የጥብቅ መከላከል ፈተና መጋፈጥ ሳይቸሉ ጨዋታው 1-0 በጦሩ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፋሲሉ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ጨዋታው የጥንቃቄ እንደሚሆን እንደገመቱ ያሰቡት እንደገጠማቸው ከተናገሩ በኋላ ጨዋታው ከባድ እንደነበር ገልፀው በጉዳት የሌሉ ተጫዋቾች አለመኖራቸው እንደጎዳቸው የፊት መስመሩ በመሳሳቱ ተጋጣሚያቸው ያገኘውን ዕድል ተጠቅሞ እንዳሸነፋቸው ተናግረዋል፡፡ ድል የቀናቸው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በተከታታይ ቡድናቸው ከጣለው ነጥብ አንፃር የሥነ ልቦና ችግር ቡድኑ ላይ መኖሩን ጠቁመው ይሄን ለማሻሻል ሦስት ነጥብ ማግኘታቸው ለዚህም ትልቅ ተጋድሎ ተጫዋቾቻቸው አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምስጋናን አበርክተዋል፡፡