ከፍተኛ ሊግ | ሻሸመኔ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከሚወዳደሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሻሸመኔ ከተማ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል፡፡

በ2014 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስር ተደልድሎ ካደረጋቸው 18 የሊጉ ጨዋታዎች በ19 ነጥቦች ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ውድድሩን የፈፀመው ሻሸመኔ ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት አስቀድሞ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥርን አከናውኗል፡፡ በዚህም መሠረት አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን በብዙሀኑ ዘንድ አግሮ በመባል የሚታወቁትን አሰልጣኝ በአንድ ዓመት ውል ሾሟል፡፡

በተጫዋችነት ዘመናቸው ለንግድ ባንክ እና ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችለው የነበሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ወደ ሥልጠናው ብቅ ካለ በኋላ የመከላከያ ሴቶች ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ፣ 2007 የኢትዮጵያ መድን ረዳት እና ዋና አሰልጣኝ እንዲሁም አቃቂ ቃሊቲን ከአንደኛ ሊግ እስከ ከፍተኛ ሊግ ድረስ ከዚህ ቀደም ማሰልጠን የቻሉ ሲሆን ቀጣይ መዳረሻቸው በኋላ በይፋ ሻሸመኔ ከተማ ሆኗል፡፡

ክለቡ የአሰልጣኙን ቅጥር ከፈፀመ በኋላ በምልመላ እና በዝውውር አዳዲስ ተጫዋቾችን በቀጣይ ቀናት እንደሚያስፈርም ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡