የዱላ ሙላቱ እና ጅማ አባ ጅፋር ጉዳይ ውሳኔ አግኝቷል

ዱላ ሙላቱ ጅማ አባ ጅፋር ‘ደመወዜን አልከፈለኝም’ በማለት ያቀረበው አቤቱታ በፌደሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ አግኝቷል።

ዱላ ሙላቱ ከመስከረም 1 2013 አንስቶ እስከ ሰኔ 30 2015 የሚያቆየው የሁለት ዓመት ውል ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የነበረው ቢሆንም ከሚያዝያ 1 2014 ጀምሮ ግን ክለቡ ደመወዙን እየከፈለው እንደማይገኝ በመጥቀስ ለፌደሬሽኑ አቤቱታውን ማስገባቱ ይታወሳል። ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጉዳዩ ዙርያ የክለቡ ኃላፊዎች የሰጡትን ምላሽ ተንተርሶ ወሳኔ ሰጥቷል።

በዚህም መሰረት ክለቡ ለተጫዋቹ ቀሪ ያልተከፈለ ደመወዙን በ7 ቀናት ውስጥ እንዲከፈል ይህንንም ተፈፃሚ ማድረግ ካልቻሉ በየዕለቱ የሚሰላ 2% መቀጮ እንዲከፍሉ የሚገደዱ ሲሆን ጉዳዩን በተቀመጠው ጊዜ መፍታት ካልቻሉ ግን የተጫዋቾች ምዝገባን ጨምሮ ከፌደሬሽኑ ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኙ መወሰኑን ጉዳዩን የያዙት የህግ አማካሪ እና ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።