በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ጠንካራ ሆነው ከቀረቡ ቡድኖች መካከል አንዱ የነበረው አርባምንጭ ከተማ የአስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የሦስት ነባሮችን ውልም አድሷል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ዘለግ ያለ ተሳትፎን እያደረገ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ካለፉትን የውድድር ዓመታት በተሻለ የተጠናቀቀውን ዓመት በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ እየተመራ ከ18 ጨዋታዎች 27 ነጥቦችን ሰብስቦ በደረጃ ሰንጠረዡ አምስተኛ ላይ ተቀምጦ መፈፀሙ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ ካለፈው በተሻለ ቁመና ላይ ዘንድሮ ለመገኘት አስቀድሞ የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድን ውል ያራዘመ ሲሆን አሁን ደግሞ አስር አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የሦስት ነባሮችን ውል በማራዘም ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ገብቷል፡፡
ቤተልሄም ዮሐንስ ቡድኑን የተቀላቀለች የመጀመሪያ ፈራሚ ሆናለች፡፡ የቀድሞው የጌዲኦ ዲላ እና አዲስ አበባ ከተማ ግብ ጠባቂ መዳረሻዋ አርባምንጭ መሆን ችሏል፡፡ አጥቂዋ ሠርካለም ባሳም ወደ ልጅነት ክለቧ ተመልሳለች፡፡ አርባምንጭን ለቃ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በድሬዳዋ ከተማ ቆይታ የነበራት አጥቂዋ ዳግም የቀድሞው ክለቧን ተቀላቅላለች፡፡ ሌላኛዋ አጥቂ ቤተልሄም ታምሩ ወደ ትውልድ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ያለፈውን ዓመት በድሬዳዋ ካሳለፈች በኋላ ነው ወደ አርባምንጭ ያመራችው፡፡
ሌላኛዋ በአዲስ አበባ ከተማ በመስመር እና በአማካይ ስፍራ ላይ ስትጫወት የምናውቃት ቤተልሄም ሰማን ፣ በአቃቂ ቃሊቲ አስደናቂ ጊዜ የነበራት አማካዩዋ ዓይናለም መኮንን ፣ ሰላማዊት ኃይሌ አማካይ ከአዲስ አበባ ከተማ ፣ መሠረት ገብረእግዚአብሔር የተከላካይ አማካይ ከአዲስ አበባ ከተማ ፣ ቤተልሄም ግዛቸው የተከላካይ አማካይ ከባህርዳር ከተማ ፣ ባንቺይርጋ ተስፋዬ ተከላካይ ከድሬዳዋ ከተማ እና ማህሌት ኃይሌ ግብ ጠባቂ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች ናቸው፡፡
ክለቡ ከአዳዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ የሦስት አማካዮችንም ውል አድሷል፡፡ ሰርካዲስ ካሳዬ ፣ የወርቅነሽ መሰለ እና ትውፊት ካዲኖን ኮንትራት ለተጨማሪ ዓመት ማራዘሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡