ከፍተኛ ሊግ | ቡታጅራ ከተማ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ስር የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ያሳለፈው ቡታጅራ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ወደ ኃላፊነት አምጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ስር ከሚደረጉ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ከሚወዳደሩ ክለቦች መካከል አንዱ ቡታጅራ ከተማ ነው፡፡

ያለፈውን የ2014 የውድድር ዘመን በምድብ ለ ስር ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች 24 ነጥቦችን ይዞ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የፈፀመ ሲሆን ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራ እንዳለ የተገለፀ ሲሆን ለዚህም አስቀድሞ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥርን ፈፅሟል፡፡ በዚህም አሰልጣኝ ያለው ተመስገን (ልቤ) የክለቡ አዲሱ አለቃ ሆኗል፡፡

በደቡብ ፖሊስ ክለብ ውስጥ በረዳት አሰልጣኝነት ረጅም ዓመታት ያሳለፈው እና አንዳንዴም ጊዜያዊ አሰልጣኝ በመሆን ጭምር ሲያገለግል የምናውቀው አሰልጣኙ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋና አሰልጣኝነት ሚናን በቡታጅራ ከተማ በማግኘቱ ለቀጣዩ አንድ ዓመት ክለቡን ተረክቧል፡፡

ክለቡ የአሰልጣኙን ቅጥር ካገባደደ በኋላ ወደ ተጫዋቾች ዝውውር ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑንም ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ መረጃው ደርሷታል፡፡