ባህር ዳር ከተማ እና እንየው ካሳሁን ጠንከር ያለ ቅጣት ተላለፈባቸው

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

አራተኛ የጨዋታ ሳምንቱን ያገባደደው የሀገሪቱ ቀዳሚ የሊግ ዕርከን ከትናንት በፊት ባስተናገዳቸው ስምንት ጨዋታዎች ላይ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ታይቶባቸዋል በተባሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ሥነ -ስርዐት ኮሚቴ ከዳኞች እና ታዛቢዎች የሰበሰበውን መረጃ ተንተርሶ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ እና ባለ ሜዳው ባህር ዳር ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ላይ የባህር ዳሮቹ የመስመር አጥቂዎች አደም አባስ እና ዱሬሳ ሹቢሳ ላይ የድሬዳዋ ከተማው የቀኝ መስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን በሰራቸው ጥፋቶች በዕለቱ ፌድራል ዳኛ ባህሩ ተካ አማካኝነት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ በቀይ መወገዱ ይታወሳል፡፡ ተጫዋቹ በዚህ ጨዋታ ላይ በሁለት ቢጫ በቀይ መውጣቱን ተከትሎ የአንድ ጨዋታ ዕግድ ሲጣልበት በተጨማሪም በተጋጣሚ ተጫዋች ላይ ምራቅ መትፋቱም በመረጋገጡ ተጨማሪ ስድስት ጨዋታ በድምሩ ሰባት ጨዋታዎች እንዲታገድ ሲወሰን የሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡

ሌላው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለገጣፎ ለገዳዲን 3-0 ሲረታ ለኤሌክትሪክ ሔኖክ አየለ የመጀመሪያዋን ጎል ካስቆጠረ በኋላ ኃይማኖታዊ መልዕክት ያለውን ፅሁፍ  ከማሊያው ስር ደርቦ በመልበሱ የሦስት ሺህ ብር ቅጣት ሲተላለፍበት ክለቡ ደግሞ የአስር ሺህ ብር በድምሩ የአስራ ሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡

ባህር ዳር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች አፀያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው እና ያልተገባ መልዕክትን ስለ ማስተላለፋቸው በተጨማሪም አንድ የክለቡ መለያ የለበሰ ደጋፊ በጨዋታ ወቅት ወደ ሜዳ ዘሎ በመግባት ሁከት ስለማስነሳቱ ሪፖርት የተደረገ በመሆኑ ክለቡ ለመጀመሪያው ጥፋት የሀምሳ ሺህ ብር እንዲሁም ለሁለተኛው ጥፋት ተጨማሪ ሀያ አምስት ሺህ ብር በድምሩ ሰባ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።

ድሬዳዋ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ክለቦች በበኩላቸው ተጫዋቾቻቸው ከአምስት በላይ ቢጫ ካርድ በማየታቸው የአምስት የአምስት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተጥሎባቸዋል፡፡

ያጋሩ