ከትናንት በስቲያ የተቋጨው የሊጉ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመንተራስ ተከታዩን ምርጥ ቡድን እና አሰልጣኝ መርጠናል።
አሰላለፍ : 4-1-3-2
ግብ ጠባቂ
ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ
ብርቱካናማዎቹ 4ኛው ሳምንት አንድ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ የፍሬው ሚና እጅግ ወሳኝ ነበር። የጣና ሞገዶቹ ጫና በበረታባቸው የሁለተኛው አጋማሽ ደቂቃዎች ያሳየው እርጋታ እና ጎል ለመሆን የቀረቡ አራት አደገኛ የግብ ሙከራዎችን ያዳነበት መንገድ በሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ አካቶታል።
ተከላካዮች
አብዱልከሪም መሐመድ – ኢትዮጵያ መድን
መድን ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያሳካ የአምበሉ ብቃት የሚደነቅ ነበር። አብዱልከሪም ዋነኛ ኃላፊነቱ የነበረውን መከላከል በመወጣት የተጋጣሚው ወላይታ ድቻ ጠንካራ ጎን የነበረውን የመስመር አጨዋወት በሚገባ ከማቆሙ በተጨማሪ ወደ ፊትም እየሄደ የማጥቃት አጨዋወቱን ሲያግዝ ታይቷል።
አሳንቴ ጎድፍሬድ – ድሬዳዋ ከተማ
በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች ከፍ ያለ ተፅዕኖ ከፈጠሩ ተከላካዮች ውስጥ ጋናዊው የድሬዳዋ ተከላካይ ተጠቃሽ ነው። ተጫዋቹ የዱሬሳ ሹቢሳን ጎል ለመሆን ምንም ያልቀረው ኳስ ከግብ አፋፍ ሲያድን በሌሎች ቅፅበቶችም ሳጥን ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔዎች ያሳለፍ የነበረበት መንገድ ቡድኑን ከተጨማሪ ጎሎች ታድጓል።
አሚኑ ነስሩ – መቻል
በጨዋታው ምንም እንኳን ፋሲሎች በተደጋጋሚ መቻል ሳጥን ውስጥ መግባት ባይችሉም ውጥረት በበዛበት ጨዋታ አሚኑ የቡድኑን መከላከል የመራበት እንዲሁም እጅግ ወሳኝ በነበሩ የጨዋታ ቅፅበቶች የፋሲል ማጥቃት ያቋርጥ የነበረበት መንገድ በቡድናችን እንዲገባ አድርጎታል።
አህመድ ረሺድ – መቻል
በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ መቻል ፋሲልን ሲረታ ጎልቶ የወጣው ሌላኛው ተጫዋች አህመድ ነው። ዘለግ ያለውን ደቂቃ ጥቃቶችን መመከት ላይ ተጠምዶ ያሳለፈው ተጫዋቹ ፋሲል ከነማ ገና በመጀመሪያው አጋማሽ እርሱ በተሰለፈበት መስመር የተጫዋች ለውጦችን እንዲያደርግ ያስገደደ ብቃትም አሳይቷል።
አማካዮች
አብነት ደምሴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ገጣፎን በረቱበት ጨዋታ አስደናቂ የመጀመሪያ አጋማሽን ያሳለፉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በጨዋታው አብነት ደምሴ አስደናቂ የቅጣት ምት ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በጨዋታው ለቡድኑ ወሳኝ የመከላከል እንዲሁም በማጥቃቱ ወቅት አጥቂዎቹን ከተቀረው የቡድን አባላት ጋር ለማገናኘት ያደረገው ጥረት ድንቅ ነበር።
ዓሊ ሱለይማን – ሀዋሳ ከተማ
ኃይቆቹ በሰራተኞቹ ላይ ባሳኩት የ4-3 ድል ውስጥ በሦስት ግቦች ላይ የተሳተፈው ዓሊ ድንቅ ቀን አሳልፏል። ኤርትራዊው አጥቂ ይበልጥ የአማካይነት ሚና በተንፀባረቀበት ጨዋታ ለመጀመሪያዎቹ ሁለትግቦች እንቅስቃሴ መነሻ ሲሆን የመጨረሻውን ግብ ደግሞ ግማሽ ሜዳ ኳስ በመንዳት እና ተጫዋቾች በማለፍ አመቻችቶ አቀብሏል።
ፎዐድ ፈረጃ – ባህር ዳር ከተማ
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በቋሚነት የተጫወተው ፎዐድ ምንም እንኳን ቡድኑ ሦስት ነጥብ ባያገኝም በግሉ በተለይ የአማካይ እና የአጥቂ መስመሩን በማገናኘት ረገድ መልካም ጊዜ ነበረው። ለመከላከል የበዛ ቦታ ሰጥተው ወደ ሜዳ የገቡትን የድሬን ተጫዋቾች ለማስከፈትም ከፍ ባለ መታተር ሲጫወት አስተውለናል።
ፀጋ ደርቤ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በቡድኑ የማጥቃት ሽግግር ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚሰጠው ፀጋ የሚደርሰውን ኳስ የተጋጣሚ የግብ ክልል በፍጥነት በማድረስ የግብ ዕድሎችን እንዲፈጠሩበት ለማድረግ ሲጥር የሚታይ ሲሆን በጣፎውም ጨዋታ የነበረው አስተዋጽኦ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት ምክንያት ሆኗል።
አጥቂዎች
እስማኤል ኦሮ-አጎሮ
እንደ ቡድን ደካማ የጨዋታ ቀን ያሳለፉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው እንደ ወትሮው ተደጋጋሚ እድሎችን መፍጠር ባይችሉም በጨዋታው አጎሮ ተሸክሟቸው ወጥቷል። በተለይም የጨዋታው ውጤት 1ለ1 በነበረበት ሂደት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምትን ተረጋግቶ ወደ ግብ የቀየረበት መንገድ የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ እንዲሆን አስችሎታል።
ሙጂብ ቃሲም – ሀዋሳ ከተማ
በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ለተከታታይ ዓመታት የማይጠፋው መጂብ የዘንድሮ አጀማመሩ ዝምታውን በወልቂጤው ጨዋታ ሰብሯል። ተጨዋቹ የመጀመሪያው ጎል ላይ ተሳትፎ የተለያየ የአጥቂ ክህሎቶቹን ያሳዩ ሦስት ዓይነት ጎሎችን ሲያስቆጥር አንድ ያለቀለት አጋጣሚም መፍጠር ችሏል።
አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን
ሊጉን በከባድ ሽንፈት የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች በቶሎ የማገገማቸው ነገር ቢያጠያይቅም አሁን ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል። ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ወላይታ ድቻ ላይ ያሳኩት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቡድኑን በሥነልቦናው ረገድ ቶሎ እንዲያገግም በማድረግ ቀላል ባልነበረው ጨዋታ ቡድናቸው በ1-0 ውጤት ሙሉ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ማድረግ በመቻላቸው የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አድርገናቸዋል።
ተጠባባቂዎች
አብበከር ኑሪ
ኢያሱ ለገሠ
ሄኖክ ኢሳይያስ
ባሲሩ ዑመር
ተስፋዬ አለባቸው
ምንያህል ተሾመ
አብዱልከሪም ወርቁ
ዱሬሳ ሹቢሳ
ጌታነህ ከበደ