የ5ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ የጨዋታ በፊት መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ያሳለፍነውን የጨዋታ ሳምንት ድል እና አቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሀዋሳ እና ድሬዳዋ የባህር ዳር ቆይታቸውን በአውንታዊ ውጤት ለመቋጨት የሚያደርጉት የ7 ሰዓት ፍልሚያ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያስመለከት ይታሰባል።
በአዳማ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ያገገሙበትን ውጤት ወልቂጤ ከተማ ላይ ያሳኩት ሀዋሳዎች በጨዋታው ያሳዩትን ጀብደኝነት በመድገም ነገም የማጥቃት አጨዋወት ላይ ትኩረት በመስጠት እንደሚንቀሳቀሱ ይታሰባል። በተለይ በጨዋታው የመስመር አጥቂ እና ተከላካዮቻቸውን ወደ ፊት በመግፋት በተደጋጋሚ የተጋጣሚን ሳጥን ለመጎብኘት ሲጥሩ ነበር። ምናልባት ድሬዳዋዎች እንደ ባህር ዳሩ ጨዋታ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው ወደ ሜዳ የሚገቡ ከሆነ ጠጣሩን የኋላ መስመር ለማስከፈት በቁጥር በዝተው ማጥቃት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ባለፈ ግን በረጃጅም ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የሚጥረውን የድሬ አጨዋወትም መመከት ይገባቸዋል።
እስካሁን ከሦስት ነጥብ ጋር መገናኘት ያልቻለው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ የመጀመሪያውን ድል ሀዋሳ ላይ በማሳካት ወደ መቀመጫ ከተማው የሚያደርገውን ጉዞ ማሳመር እያሰበ ወደ ሜዳ ይገባል። በ4ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው ቡድኑ በጨዋታው ጠንከር ያለ ጫና ቢገጥመውም የጎል ቅድሚያ ወስዶ ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ሲጥር ነበር። ከግማሽ ሰዓት በላይም በጎዶሎ ተጫዋች ተጫውቶ በጠንካራ የመከላከል አጨዋወት በተከላካዮቹ እና ግብ ዘቡ ብቃት አንድ ነጥብ ይዞ ወጥቷል። ይህ የመከላከል አጨዋወት የሚደነቅ ቢሆንም በማጥቃቱ ረገድ ያለበትን ውስንነት ግን ማሳደግ ይጠበቅበታል። እንደገለፅነው ተናፋቂዋን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ጎል ፊት በተደጋጋሚ መገኘት ስለሚገባ በየጨዋታው ግቦችን እያስተናገደ የሚገኘው ሀዋሳ ለመፈተን መጣር ይገባዋል።
ኃይቆቹ መጠነኛ የሆድ ህመም ላይ የሚገኙት ዓሊ ሱሌይማን እና ዳንኤል ደርቤን የመጠቀማቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ብርትካናማዎቹ በበኩላቸው የ7 ጨዋታዎች ቅጣት የተጣለበት እንየው ካሣሁንን ግልጋሎት ብቻ ያጣሉ።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 19 ጊዜ ሲገናኙ ሀዋሳ ሰባት ድሬዳዋ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል አድርገው በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ኃይቆቹ 18 ጎሎችን ሲያስመዘግቡ ብርቱካናማዎቹ 16 ጎሎች አሏቸው።
የሳምንቱን የመክፈቻ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ዳንኤል ግርማይ ሲመራው ሙሉነህ በዳዳ እና ታምሩ አደም ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ከተማ
ባሳለፍነው ሳምንት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ያሳካው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባገኘው የአሸናፊነት ጎዳና ለመቀጠል በተቃራኒው አዳማ ከተማ ደግሞ በሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ ወደ ሊጉ አናት ከፍ ለማለት የሚያደርጉት ግብ ግብ ቀልብን እንደሚስብ ይታሰባል።
አብረውት ወደ ሊጉ ካደጉት ለገጣፎ ለገዳዲ ጋር የ4ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያደረጉት ኤልፓዎች በጨዋታው ያሳዩት ያልተጠበቀ ብቃት ብዙዎችን አስገርሟል። በአብዛኛው ከኳስ ጋር ምቾት ያላቸውን ተጫዋቾች በቀዳሚው አሰላለፍ በማስገባት በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያስመለከቱን ዓላማ ያለው የኳስ ቁጥጥር እና የጥቃት ሂደቶች አንጋፋውን ክለብ ዳግም እንድናስታውስ አድርጎናል። ምናልባትም ነገም ይህ ድፍረት የሚደገም ከሆነ በአማካይ መስመር ላይ የአብነት፣ምንያህል እና ስንታየሁ ጥምረት ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ሚኪያስ፣ ሔኖክ እና ፀጋ ጋር ተደምሮ ለአዳማዎች ፈተናን ሊቸር ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን የአዳማን ፈጣን የመስመር ጥቃቶች መመከቻ መላ መዘየድ የግድ ይላቸዋል።
በብዙ መስፈርቶች ተሻሽሎ የዘንድሮውን የውድድር ዘመን የጀመረው አዳማ ከተማ ጠንከር ያሉ መርሐ-ግብሮችን እየተጋፈጠ ቢሆንም በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የተሟላ ቡድን ይመስላል። በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ገና በጊዜ ወሳኙን ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን በጉዳት ያጣው ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ መሰረቱ ይናጋል ተብሎ ቢሰጋም በቡድናዊ መዋቅር የአንድን ተጫዋች ቦታ የሸፈነበት መንገድ የሚደነቅ ነው። በማጥቃቱም ረገድ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሽግግሮች ግብ ለማግኘት የሚጥርበት መንገድ መልካም ነው። ምባልባት ኤልፓ እንደ ጣፎው ጨዋታ ኳስ ይዞ የሚጫወት ከሆነ በቀጥተኛ አጨዋወት የጨዋታውን ውጤት ለመወሰን እንደሚጥር ይገመታል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን አዳማ ከተማ ግን ሁለቱን ቀዳሚ የመሐል ተከላካዮቹን ሚሊዮን ሰለሞን በጉዳት አዲስ ተስፋዬን ደግሞ በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀምም።
ዮናስ ካሳሁን የጨዋታው የመሐል አልቢትር ሲሆኑ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ እና አሸብር ታፈሰ ረዳት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ደግሞ አራተኛ ዳኛ እንደሆኑ ታውቋል።