ሰበታ ከተማ ዕግዱ ተነስቶለታል

ከተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበት የነበረው ሰበታ ከተማ ጊዜያዊ መፍትሔ አግኝቷል።

ከ2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የሊግ እርከን ሲወዳደር የነበረው ሰበታ ከተማ ዓምና ከሊጉ ተሰናብቶ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ይታወቃል። የቀድሞ የክለቡ 14 ተጫዋቾች ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ባቀረቡት ክስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ ክለቡ በተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ እንዳይሳተፍ እና ፌዴሬሽኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንዳያገኝ ከነሐሴ 30 2014 ጀምሮ የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበት እንደነበር ዘገባ ማቅረባችን አይዘነጋም።

አሁን የተጫዋቾቹ ሕጋዊ ጠበቃ እና ወኪል ከክለቡ ጋር ተጫዋቾቹ የደረሱበትን የዕርቅ ውል ስምምነት ደብዳቤ በማያያዝ ለፌዴሬሽኑ በማስገባት ክለቡ ለተጫዋቾቹ መክፈል የሚጠበቅበትን ክፍያ በሦስት ዙር እስከ ጥር ወር ከፍሎ ለማጠናቀቅ ስምምነት ላይ የደረሰ በመሆኑ ዕግዱ እንደተነሳለት የተጫዋቾቹን ጉዳይ ከያዙት የሕግ ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።