ሪፖርት | ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ነጥብ ተጋርተዋል

የአምስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ በሀዋሳ እና ድሬዳዋ መካከል ተከናውኖ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ከመጨረሻ ጨዋታቸው አንፃር የሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ወልቂጤ ከተማን ሲረቱ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ሰለሞን ወዴሳን በላውረንስ ላርቴ ፣ ብርሀኑ አሻሞን በአብዱልባሲጥ ከማል ሲተኩ ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ለጨዋታው በቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በኩል በቅጣት በሌለው እንየው ካሳሁን ምትክ መሀመድ አብዱለጢፍን ፣ በብሩክ ቃልቦሬ ከቅጣት በተመለሰው ኤልያስ አህመድ በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን በመያዝ ሀዋሳዎች በተሻሉበት እና የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች የሚሰሩትን የቅብብል ስህተት ለመጠቀም ድሬዳዋ ከተማዎች የጣሩበትን የመጀመሪያው አጋማሽ አስመልክቶናል፡፡ ከመሀል ክፍሉ ከሚገኙ ኳሶች ዕድሎችን ለመጠቀም ወደ ቀኝ መስመር በዓሊ ሱለይማን አማካኝነት ለማጥቃት ኃይቆቹ ጥረት ማድረግ ቢችሉም የመጨረሻው ሳጥኑ አካባቢ የሚታይባቸው ደካማ የአጨራረስ ክፍተት በተቃራኒው ግብ እንዲቆጠርባቸው ሆኗል፡፡

በዚህም አማካዮች እና ተከላካዮቻቸው በቅብብል ወቅት የሚፈጥሩትን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ብርቱካናማዎቹ ቀዳሚውን ግብ አግኝተዋል፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳው ተከላካይ በረከት ሳሙኤል አጠገቡ ለነበረው አብዱልባሲጥ ከማል ኳስን አቀብላለው ብሎ በተሳሳተ አድራሻ ለያሬድ ታደሰ አቀብሎት አማካዩ ምቹ ቦታ ለነበረው ቢኒያም ጌታቸው ሰጥቶት አጥቂው ወደ ሳጥኑ ሁለቴ ገፋ ካደረገ በኋላ በግራ እግሩ አስቆጥሮ ድሬዳዋን መሪ አድርጓል፡፡ ተጫዋቹ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን በእምባ ታጅቦ ገልጿል፡፡

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በተረጋጋ የጨዋታ መንገድ ለመጫወት በተወሰነ መልኩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ሀዋሳዎች አቻ መሆን ችለዋል፡፡ 30ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ የድሬዳዋ የግብ አቅጣጫ በኤፍሬም አሻሞ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በቃሉ ገነነ ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ጋናዊው ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ የፍሬው ጌታሁንን የአቋምም ስህተት ተመልክቶ በግንባር ገጭቶ ከመረብ በማሳረፍ ሀዋሳን ወደ ጨዋታ መልሷል፡፡

ነገር ግን ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል በዚሁ ውጤት ያመራል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት አሁንም የቅብብል ስህተታቸውን ማረም የተሳናቸው ሀዋሳዎች ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል፡፡ 45ኛው ደቂቃ ላይም አቤል አሰበ ከሀዋሳ አማካዮች የተቋረጠን ኳስ አግኝቶ መሀል ለመሀል ለቢኒያም ጌታቸው ሲያቀብለው የመሀል ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል በድጋሚ የታየበትን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት በአግባቡ ተጠቀሞ ቢኒያም ለድሬዳዋም ሆነ ለራሱ ሁለተኛ ጎል ከመረብ አዋህዶ 2-1 በምስራቁ ክለብ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በመጀመሪያው አጋማሽ ለተከላካዮች በቂ ሽፋን የሚሰጥ ተጫዋች ያልነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ጋዲሳ መብራቴን በዮሴፍ ዮሐንስ ተክተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል፡፡ ፈጠን ባለ የማጥቃት ኃይል ጨዋታቸውን የጀመሩት ሀዋሳዎች ከዓሊ ሱለይማን ከመስመር በተሻገረ ኳስ ሙጂብ ቃሲም አግኝቶ ቢመታም አሻንቲ ጉድፍሬድ ኳስን ባወጣትበት ቅፅበት አጋማሹ ጅምሩን አድርጓል፡፡ ቀዝቀዝ ባለ የሜዳ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች አሁንም የሳጥን ውስጥ ችግራቸውን መቅረፍ ያልቻሉበት በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ይበልጥ የጥቃት መንገዳቸውን ቢኒያም ጌታቸው ላይ አድርገው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተንፀባርቋል፡፡

የሚባክኑ ኳሶች የተበራከቱበት እና የተገደቡ እንቅስቃሴዎች ረጅሙን ደቂቃ በርከትው ያየንበት ሁለተኛው አርባ አምስት በተለይ የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ሀዋሳዎች ባደረጉት ብርቱ ትግል በስተመጨረሻን ነጥብ የተጋሩበትን ጎል አግኝተዋል፡፡ 88ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የተገኘን አጋጣሚ በቃሉ ገነነ በቀጥታ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ሲያሻማ ተቀይሮ የገባው እዮብ አለማየሁ ከድሬዳዋ ተከላካይ ጋር ታግሎ የሰጠውን ኳስ ዓሊ ሱለይማን ሀዋሳን ወደ 2-2 አቻ ውጤት ያሸጋገረች ግብን አስቆጥሯል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በጭማሪ ሽርፍራፊ ሰከንድ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች የቅጣት ምት አግኝተው መሀመድ አብዱለጢፍ አክርሮ መትቶ የላይኛው የግቡ ብረት ከመለሰ በኋላ ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በእንቅስቃሴ ጥሩ መሆናቸውን ጠቁመው በመከላከሉ ረገድ ግን መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ካሉ በኋላ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ ድሬዳዋ ላይ በሚደረገው ውድድር የተሻሉ ሆነው ለመቅረብ እንደሚጥሩ ገልፀዋል፡፡ ረጅሙን ደቂቃ ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻም አቻ ለመሆን የተገደዱት የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በጨዋታው ጥሩ እንደነበሩ ተናግረው በእግር ኳሱ ከሚያጋጥሙ ነገሮች አንዱ እንደገጠማቸው ጠቁመው በተከላካይ እና ግብ ጠባቂ ስህተት ውጤት እየተገባቸው ለማጣት እንደተገደዱ ገልፀዋል፡፡