ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ሳይሸናነፉ ቀርተዋል

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በአዳማ ከተማ መካከል ተካሂዶ 2-2 ተጠናቋል።

የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድሉን ለማግኘት በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና የሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለገጣፎን ለገዳዲን ከረታው ስብስቡ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት በኋላ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች አዲስ ተስፋዬ ፣ ሚሊዮን ሰለሞን እና አሜ መሐመድን በታዬ ጋሻው ፣ ዳንኤል ደምሴ እና ዊልያም ሰለሞን በመተካት በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተዋል።

ጥሩ ፉክክር እንደሚያስመለክተን በተጠበቀው በዚህ ጨዋታ ጠንከር ያለ የጎል ሙከራ መመልከት የጀመርነው ገና ከጨዋታው መጀመርያ በአንደኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከሳጥን ውጪ በምንያህል ተሾመ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ ያገኘውን ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ በቀጥታ ቢመታውም የኢትዮ ኤሌክትሪክ የግብ ዘቡ ዘሪሁን ታደለ አምክኖበታል። 

በዚህ ሙከራ መነሻነት የጨዋታው ሂደት እየተነቃቃ ሳቢነቱን ቀጥሎ ይጓዛል ቢባልም መሀል ሜዳ ላይ የሚደረጉ ቅብብሎች ወደ ፊት በመሄድ ለአጥቂዎቻቸው የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠሩ በኩል ውስንነቶች በመኖራቸው ምክንያት ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የሰላ ሙከራዎችን ሳያስመለክቱን ቆይተዋል።

በጨዋታው 31ኛው ደቂቃም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የመጀመርያ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል። በዚህም በረጅሙ የተላከውን ኳስ የአዳማው ግብ ጠባቂ ኳሱን በተገቢ ሆኔታ ባለመቆጣጠሩ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ፀጋ ደርቤ አመቻችቶ ያቀበለውን ሄኖክ አየለ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ ራሳቸው በፈጠሩት የቅብብል ስህተት በምላሹ አዳማዎች የአቻነት ጎል በ34ኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል።

ከግራ መስመር የተነሳውን ኳስ አብዲሳ ጀማል ያቀበለውን አንጋፋው አማካይ መስዑድ መሐመድ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ በመምታት ባስቆጠረው ጎል ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በቀሩት ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ወደ ማጥቃት ሽግግር ሲገቡ ከጨዋታ ውጪ እንቅስቃሴ መቆጣጠር በለመቻላቸው ሌሎች የጎል ዕድሎችን ሳንመለከት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛውን አጋማሽ ጅማሮ በጉዳት ምክንያት ዳዋ ሆቴሳን ለመለወጥ የተገደዱት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የፊት መስመራቸው ይሳሳል ቢባልም የታየው በተቃራኒው ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን የቀጠሉት አዳማዎች 58ኛው ደቂቃ አማኑኤል ጎበና ከሳጥን ውጭ በመምታት ኳስና መረብን አገናኘ ሲባል ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ቢያድንበትም በ63ኛው ደቂቃ መሪ መሆን የቻሉበትን ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። ከቀኝ መስመር የተነሳውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አሜ መሐመድ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን አብዲሳ ጀማል አግኘቶ በጥሩ አጨራረስ የቡድኑን መሪ ያደረገች ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ እጅግ ተዳክመው የመጡት ኤልፓዎች የአዳማን የማጥት ጫና መቋቋም አቅቷቸው አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት እና ወደ ጨዋታው ለመግባት ከተጫዋቾች ቅያሪ ውጨ የረባ ነገር ማድረግ አልቻሉም። ደቂቃ እየገፋ ሄዶ አዳማዎች ሦስተኛ ጎል ለማግኘት በአሜ መሐመድ እና አብዲሳ ጀማል አማካኝነት ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም። የጨዋታው መጠናቀቂያ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩት የተነቃቁት ኤልፓዎች ከቅጣት ምት ኳስ በአንዳልጋቸው ይልሀቅ የግንባር ኳስ ሙከራ በኋላ 84ኛው ደቂቃ የአቻነት ጎል አግኝተዋል።

መነሻውን ከቅጣት ምት ያደረገውን ኢብራሂም ከድር ያሻገረለትን በቁመት ዘለግ ያለው አማካይ አብነት ደምሴ ኳሱ አየር ላይ እያለ ደገፍ በማድረግ ቡድኑን ከሽንፈት የታደገች ወሳኝ ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። በቀሪ ደቂቃዎች ሌላ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠር ጨዋታው በሁለት አቻ ውጤት ተገባዷል።

የባህር ዳር ቆይታቸውን አምስት ነጥብ በመያዝ ያጠናቀቁት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ወደፊት ብዙም ባይሄዱም ከዕረፍት በፊት በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ እንደነበሩ ተናግረው በሁለተኛው አጋማሽ በአዳማ ብልጫ የተወሰደባቸው ቢሆንም የአቻነቱን ሁለተኛውን ጎል በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። አክለውም የአዳማ ከተማን ጥንካሬ ሳይሸሽጉ ገልፀዋል።

በአምስት ጨዋታ ሰባት ነጥብ በመያዝ ወደ ድሬደዋ የሚጓዙት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው በመጀመርያው አጋማሽ ኳስ በመንጠቅ በኩል እንደ ቡድን በህብረት ሳይሆን በተናጠል ማድረጋቸው ብልጫ እንዲወሰድባቸው እንዳደረጋቸው ገልፀው ከፊት ያሉት አጥቂዎች እርጋታ ኖሯቸው ከአማካይ ተጫዋቾች ጋር ተናበው በአዕምሮ ቢጫወቱ በርከት ያሉ ጎሎችን ማስቆጠር እንደሚችሉ ሀሳብ ሰጥተው። በማስከተልም “ተጫዋቾች በሜዳ ላይ በተከታታይ መውድቅ ሊወገድ ይገባል” ሲሉ “ሜዳ ላይ መተኛት ልምምድ አይደለም ለተመልካቾች ክብር ሊሰጥ ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።