መረጃዎች | 18ኛ የጨዋታ ቀን

የ5ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

የጨዋታ ሳምንቱን ተጠባቂ ፍልሚያ የተመለከተ ሰፊ ዘገባ ከቆይታ በኋላ የምናቀርብ ሲሆን በዕለቱ ከሽንፈት መልስ የሚገናኙት ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታም ጠንከር ያለ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። በተለይ ቡድኖቹ ከሚገኙበት አሉታዊ ወቅታዊ አቋም ወትቶ ወደ ቀጣዩ የሊጉ የውድድር ከተማ ለማምራት የሚያደርጉት ግብ ግብ የተናፋቂው ጨዋታ ጥሩ ማሟሻ እንደሚሆን ይገመታል።

የሊጉን የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ረተው በተከታታይ በሁለቱ እጅ የሰጡት ወልቂጤ ከተማዎች በሀዋሳው ጨዋታ በብዙ መስፈርቶች የተሻሉ የነበረ ቢሆንም የኋላ መስመራቸው ግን ክፍተቶችን ሲሰጥ አስተውለናል። በተለይ የመሐል ተከላካዩ ቴዎድሮስ ሀሙ ገና በ7ኛው ደቂቃ ተቀይሮ መውጣቱ እና ውሀብ አዳምስ ከዚህ ቀደም በነበረው ብቃት ላይ አለመገኘቱ የቡድኑን አጥር አሳስቶት ነበር። የነገ ተጋጣሚው ሲዳማ ደግሞ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ማጥቃት ላይ ያተኮረ አጨዋወት ሊከተል ስለሚችል ይህ ችግሩ መልሶ እንዳያገረሽ መጠንቀቅ የግድ ይለዋል። በተቃራኒው በፈጣን ሽግግር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሲዳማዎች ፈተና ሊሆን ይችላል።

የአሠልጣኝ ለውጥ እስከ ማድረግ ያስገደደው አስከፊ አጀማመር በሊጉ ያደረገው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ባሳለፍነውም ሳምንት ከሦስት ነጥብ ጋር ባይገናኝም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ከከዚህ ቀደም ፍልሚያዎቹ የተሻለ ነገር አሳይቷል። በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ መሻሻል ቢያሳይም ግን ዕድሎችን በአግባቡ የመጠቀም ክፍተት ታይቶበታል። ይህንን የአጨራረስ ውስንነት በማስተካከልም ከድል ጋር ለመታረቅ እንደሚጥር ይገመታል። በተቃራኒው ግን በአራቱ ጨዋታዎች በአማካይ በየጨዋታው ሦስት ሦስት ግቦችን እያስተናገደ የሚገኘው የኋላ መስመሩ ነገም ዋጋ እንዳያስከፍለው መጠንቀቅ ይሻዋል። ከላይ እንደገለፅነውም የወልቂጤን ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮች መመከቻ መላ መዘየድም የግድ ይለዋል።

በጨዋታው ወልቂጤ ከተማ የአምስት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ግልጋሎት አያገኝም። በዚህም ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ፣ አፈወርቅ ኃይሉ፣ ጀማል ጣሰው እና ጌታነህ ከበደ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ናቸው። ሲዳማ ቡና በበኩሉ ነገም አምበሉን ሳላዲን ሰዒድ እንደማያገኝ ተረጋግጧል። ከዚሁ ከሲዳማ ቡና ጋር ተያይዞ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ይህን ጨዋታ በቴክኒክ ቦታ ላይ ሆነው ለመምራት የወረቀት ጉዳዮቻቸው እስከ አሁን ያልተገባደደላቸው ሲሆን ምናልባት ግን ነገ በጊዜ የሚጠናቀቅ ከሆነ ሊመሩ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ የ1ለ0 ድል ሦስቱን ጨዋታዎች ሲያሸንፍ አንዱን ጨዋታ ደግሞ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ሲመራው ለዓለም ዋሲሁን እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ረዳት ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።