ያለፉት ሁለት ዓመታት የሊጉ አሸናፊዎችን የሚያገናኘውን የነገውን ተጠባቂ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ፋሲል ከነማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መድረክ ከመጣበት የ2009 የውድድር ዓመት ጀምሮ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የትኩረት ደረጃቸው ከፍ እያለ መጥቷል። በተለይም ፋሲል ከነማ ዋንጫውን ባነሳበት 2013 እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ክብር ከቆይታ በኋላ ባስመለሰበት 2014 ይህ መርሐ ግብር የትኩረት ማዕከል ሆኗል። ዘንድሮም ምንም እንኳን ውድድሩ እምብዛም ሳይከር 5ኛው ሳምንት ላይ የተገናኙ ቢሆንም ከአህጉራዊ ውድድሮች የተመለሱት ጊዮርጊስ እና ፋሲል በዋንጫ ፍልሚያው ውስጥ ተገማችነታቸው እንዳለ መሆኑ የነገውን ግጥሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል።
ፈረሰኞቹ ከ2006 ወዲህ ድንቅ የሚባል አጀማመር አድርገዋል። አራት ጨዋታዎችን አድርጎ ከሁሉም ሙሉ ነጥብ የሰበሰበው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ የተፈተነባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ነጥብ ለመጣል ግን አልተገደደም። በአንፃሩ ከሴፋክሲያን ጋር የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የደርሶ መልስ ጨዋታ የነበረበት ፋሲል ከነማ ካደረጋቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ብቻ አሳክቷል። ውድድሩ ሲጀምር አዳማን 2-1 መርታት ችለው የነበሩት አፄዎቹ በመቻል ደግሞ የ1-0 ሽንፈት አግኝቷቸዋል።
የሁለቱ ቡድኖች የሊግ አጀማመር በራሱ በነገው ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይገመታል። ካሁኑ 15 ግቦችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ ያሳረፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት የአሸነፊነት ሥነልቦና መሰል ትልልቅ ጨዋታዎችን አሸንፎ ለመውጣት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንለት ዕሙን ነው። በአንፃሩ ፋሲል ከነማ አህጉራዊ ውድድር ላይ መቆየቱ ወደ ሊጉ መንፈስ ለመመለስ ጊዜ እንዲወስድበት ያደረገ ይመስላል። በተለይም በመቻሉ ጨዋታ ቡድኑ ያሳየው አቋም ከተጠባቂነቱ አኳያ ሲታይ ከነገው ጨዋታ በፊት ሊገኝበት ከሚፈልገው ደረጃ ጋር የሚነፃፀር አይደለም። ሆኖም አምና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ 26 ጨዋታዎች በኋላ ከሽንፈት ጋር እንዲገናኝ ያደረገው የአፄዎቹ አዕምሯዊ ጥንካሬ በመሰል ትልልቅ አጋጣሚዎች ላይ ሊመለስ እንደሚችል ማሰብም ይቻላል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከፍ ባለ ጉልበት ጨዋታዎችን የሚጀምሩበትን አኳኋን በተለይም በመድን እና በሲዳማ ላይ በድምሩ ከዕረፍት በፊት ሰባት ጎሎችን ያስገኛላቸው እንደመሆኑ ነገም በተመሳሳይ ግለት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል። ይህንን ግፊት ማርገብ እና በፈጣን ጥቃቶች ምላሽ መስጠት ደግሞ ከአፄዎቹ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በዚህም በሽግግሮች ውስጥ ማን ቀድሞ የማንን የተከላካይ መስመር አደረጃጀት በማለፍ ከግብ አፋፍ ይደርሳል የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ተጠባቂ ነው።
ከመቻሉ ጨዋታ አንፃር ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን መልሰው የሚያገኙት አፄዎቹ በተለይም ከወገብ በላይ ያለው የቡድናቸው ክፍል አፈፃፀም ተሻሽሎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ይህም ቡድኑ ፈጠን ያለ ስኬታማ ቅብብሎችን በመከወን ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረሱ በኩል የታየበትን ክፍተት እንዲቀርፍ በር ይከፍታል። በተለይም ከግራ እና ከቀኝ የሚነሱት አማካዮች በጨዋታው ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም። ይበልጥ በአመዛኙ ከቀኝ የሚነሳው ሽመክት ጉግሳ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ የግራ መስመር ጥቃት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ያለው ረመዳን የሱፍ የሚገናኙባቸው ቅፅበቶች አንዳች ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ።
ፈረሰኞቹ ከአዲስ ፈራሚያቸው ዳዊት ተፈራ ያገኙትን የጨዋታ ማቀጣጠል ብቃት በጉዳት ምክንያት አጥተውታል። ቡድኑ ከተከላካይ መስመር ፊት በአማራጮች ከሚፈጥረው የሁለትዮሽ ጥምረት መካከል ለአንደኛው በተለይም ከበረከት ደልዴ ጋር ለሚጣመረው አማካይ (ናትናኤል ዘለቀ ወይም ጋቶች ፓኖም) ወደ ፊት ገፍቶ የመጫወት ነፃነት ክፍተቱን ለመሙላት ትልቅ ዕገዛ ይኖረዋል። ይህን አካሄድ ከቢኒያም በላይ ክህሎት እንዲሁም ከግራ እና ቀኝ የሚነሱ የማጥቃት ሚናቸው የጎላ ተሰላፊዎቹ በተለይም ከቸርነት ጉግሳ ጋር ሲያጣምር የቡድኑ የፈጠራ አቅም ከፍ ብሎ ይታያል። ይህ መዋቅር ከፋሲል ከነማ አንፃር ሲታይ በይሁን እንዳሻው ግራ እና ቀኝ ባሉ ቦታዎች ላይ የሚኖረው ስኬት በአፄዎቹ ቀሪ አማካዮች የሽግግሮች ትጋት ላይ የሚመሰረት ቢሆንም በቦታው የሚኖረው ፍልሚያው ግን በጨዋታው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም።
15 ግቦችን ከሰባት ተጫዋቾቻቸው ያስቆጠሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጎሎችን የማግኘት አማራጫቸው ሰፊ ሆኖ ይታያል። ከሁሉም ቀድሞ ግን የሚጠቀሰው ቶጓዊው አጥቂ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ነው። በአማካይ በየ40 ደቂቃው አንድ ጎል እያስቆጠረ የሚገኘው አጥቂው በነገውም ጨዋታ የትኩረት ነጥብ መሆኑ አያስገርምም። ከአፄዎቹ የመሀል ተከላካይ ጥምረት እና በሴፌክሲያኑ የመልስ ጨዋታ ያሳየውን ድንቅ ብቃት ለመድገም ከሚያልመው ሚኬል ሳማኬ ጋር የሚኖረው ትንቅንቅም ሌላኘው የነገው ጨዋታ ተጠባቂ ሁነት ነው። በአንፃሩ ካለፉት ዓመታት አኳያ አሁንም ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ለሚፈልጉት ፋሲል ከነማዎች የፊት መስመር ተሰላፊዎች ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ ስለመሆናቸው ለማሳየት ከነገ የተሻለ መድረክ የሚያገኙ አይመስልም።
ከእነዚህ እና ከሌሎች የሜዳ እና የሜዳ ውጪ ነጥቦች አኳያ አጓጊ በሆነው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ሱራፌል ዳኛቸውን በጉዳት ሲያጣ በአንፃሩ በዛብህ መለዮ ከጉዳት ይመለስለታል፡፡ በሌላ በኩል መናፍ ዐወል በጉዳት መሰለፉ አጠራጣሪ ሲሆን ሽመክት ጉግሳ ከቅጣት መልስ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ጉዳት ላይ የቆየው ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሐንስ እና ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የሚርቀው ዳዊት ተፈራ ከፋሲሉ ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ወደ ልምምድ የተመለሰው አቤል ያለውም ለነገ አይደርስም።
ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ 11 ግንኙነቶችን አድርገዋል። ሁለት ጊዜ ብቻ ነጥብ ሲጋሩ ፋሲል አምስት ፣ ጊዮርጊስ ደግሞ አራት ድሎችን አስመዝግበዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 27 ጎሎች ውስጥ 15ቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ 12ቱ ደግሞ በፋሲል ከነማ ስም የተመዘገቡ ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚሌኒየሙ የ2-0 ፋሲል ከነማ ደግሞ 2011 ላይ የ3-0 የፎርፌ ውጤቶችን አግኝተዋል።
ተጠባቂው ጨዋት በኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ አማካይነት ሲመራ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና አበራ አብርደው በረዳትነት እንዲሁም አራተኛ ዳኛ በመሆን ተካልኝ ለማ ተመድበዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኬ
ዓለምብርሀን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – ታፈሰ ሰለሞን – በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
ፍቃዱ ዓለሙ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ቻርለስ ሉኩዋጎ
ሱለይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ረመዳን የሱፍ
ጋቶች ፓኖም – በረከት ወልዴ
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ቢኒያም በላይ – ቸርነት ጉግሳ
ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ