ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

የእንዳለ ከበደ ብቸኛ ግብ ሲዳማ ቡናን በባህር ዳር የመጨረሻ ጨዋታው ከድል ጋር አገናኝታለች።

ወልቂጤ ከተማ ከሀዋሳ ከተማው ጨዋታ አንፃር ባደረጋቸው አራት ለውጦች ብርሀኑ ቦጋለ ፣ ተመስገን በጅሮንድ ፣ ፋሲል አበባየሁ እና አቡበከር ሳኒን በቴዎድሮስ ሀሙ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ አቤል ነጋሽ እና ጌታነህ ከበደ ቦታ ተጠቅሟል። በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ የተጠቀሙበት ቀዳሚ አሰላላፍ ሳይቀይሩ ገብተዋል።

የሲዳማ ቡና የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በተሻለ ማየል በቻለበት እና ብዙም የጠሩ አጋጣሚዎችን ለመመልከት በቂ ዕድሎችን ባላገኝንበት ቀዳሚው አርባ አምስት ወልቂጤ ከተማዎች መሀል ሜዳው ላይ ብልጫ ለመውሰድ ለመንቀሳቀስ ቢችሉም ከተሻጋሪ እና ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶችን ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ሲዳማዎች በተደጋጋሚ በመስመር እና በቀጥተኛ ኳሶች ይገዙ ቦጋለ እና ወደ ቀኝ መስመር በኩል ወደ ቡልቻ ሹራ ተጠግተው ሲጫወቱ ቢታዩም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ግን ደካሞች ነበሩ፡፡

በአንፃሩ በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ያጡት እና በይበልጥ አማካዩ ብዘአየው ሰይፉ ላይ የተንጠለጠለ የአጨዋወት መንገድ ሲያደርጉ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በጨዋታው ጅማሮ በብዙአየሁ አማካኝነት በሙከራ ረገድ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በሂደት ግን ተገድበው ታይተዋል፡፡ ይገዙ ቦጋለ በረጅሙ 18ኛው ደቂቃ ላይ የተሻገረለትን ኳስ ከግቡ ትይዩ ተገናኝቶ አስቆጠረው ሲባል ወደ ላይ ሰዶታል፡፡ ሌላኛዋ ሙከራ ቡልቻ ሹራ ግብ አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም በዕለቱ ረዳት ዳኛ ከጨዋታ ውጪ የተባለችው እና በጨዋታው መገባደጃ ከቅጣት ምት ይገዙ አክርሮ መትቶ ሮቨርት የያዘበት የጨዋታው ጥቂት ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መሀል ሜዳ ላይ የተረጋጋ ቅርፅ ለመያዝ በማሰብ ሲዳማ ቡናዎች አቤል እንዳለን በሙሉቀን አዲሱ ለውጠው በይበልጥ በተሻለ መንቀሳቀሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው የሲዳማን የኳስ ቅብብል ስህተት በመጠቀም ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ተፅዕኖ ለመፍጠር ቢጥሩም የሲዳማ የግብ አቅጣጫ አካባቢ ሲደርሱ ግን ደካሞች ሆነው ታይተዋል፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይ መሀሪ መና ከግራ የወልቂጤ አቅጣጫ የተገኘን ኳስ በቀጥታ አክርሮ መቶ ሮቨርት ኦዶንካራ በመለሰበት ሙከራ ሲዳማዎች ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል፡፡ የሲዳማ ተጫዋቾች በቅብብል ወቅት በሰሩት ስህተት የወልቂጤው ተመስገን በጅሮንድ እግር ስር የደረሰችን ኳስ አማካዩ በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ ፊሊፕ ኦቮኖ እንደምንም ወደ ውጪ አውጥቷታል፡፡

ወደ ሳጥን በመድረሱ ረገድ መቸገር ባይችሉም የአጨራረስ ድክመት በደንብ ይስተዋልባቸው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች የተጫዋቾች ለውጥ ካደረጉ በኋላ ኃይላቸውን በማሳደግ ጎል ማስቆጠር ችለዋል፡፡ 76ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ያኩቡ መሀመድ አክርሮ መትቶ በጉዳት በወጣው ሮቨርት ኦዶንካራ የተተካው ጀማል ጣሰው በሚገርም ብቃት ኳሷን አውጥቶበታል፡፡ በሌላ ሙከራም ከሳጥን ውጪ ፍሬው ሰለሞን መትቶ ጀማል ጣሰው ከመለሰበት በኋላ 81ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ጋር ኳስን አገናኝተዋል፡፡ በረጅሙ ከመሀል ሜዳ የተሰጠውን ናይጄሪያዊው ጉድዊን ኦቫጄ ወደ ጎል ሲያሻግር በቅርበት የነበረው እንዳለ ከበደ ወደ ጎልነት ቀይሮ ሲዳማን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ጨዋታውም በቀሩት ደቂቃዎች ግቦችን ሳያስመለክተን 1-0 በሲዳማ ቡና ድል ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የሲዳማ ቡናው ረዳት አሰልጣኝ ቾንቤ ገብረህይወት ጨዋታው ጥሩ እንደነበር እና ከባለፈው ጨዋታ በተሻለ መንቀሳቀሳቸውን ከጠቆሙ በኋላ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ጎሎ ቶሎ ቶሎ ደርሰው ዕድሎችን መጠቀም አለመቻላቸውን እና ከዕረፍት መልስ ተጫዋቾች በተነገራቸው መጠን ውጤት እንደተገኘ ገልፀዋል፡፡ ተከታታይ ሽንፈት የገጠመው ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በአንፃራቸው በቡድኑ ላይ የነበረው የተጫዋቾች ጉዳት ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ገልፀው ጨዋታውን በጥንቃቄ ለመጫወት አቅደው ከዕረፍት በፊት ያገኙትን ዕድል አለመጠቀማቸውን ጠቁመው በተሰራ ስህተት ለሽንፈት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ያጋሩ