የሜዳ ላይ ጉሽሚያ በዝቶበት በከፍተኛ ግለት የተካሄደው ተጠባቂ ጨዋታ በዐፄዎቹ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።
ፋሲል ከነማ ከመቻል ሽንፈት ለማገገም ወንድማገኝ ማርቆስን በሽመክት ጉግሳ ብቻ በመተካት ሜዳ ሲገባ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን ድል ካደረገው ስብስቡ ምንም ዓይነት የተጫዋች ለውጥ ሳያደርግ ለጨዋታው ቀርቧል።
በኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ የተመራው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የሜዳ ላይ ፉክክሩ ከአስደማሚ የደጋፊዎች ድባብ ጋር ተከናውኗል። መሐል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥሩን በበላይነት ለመቆጣጠር በሚደረግ ትንቅንቅ ጨዋው ቀጥሎ ወደ ጎል በመድረስ ቀዳሚዎቹ ፈረሰኞች ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ የፋሲል ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት እንዲሁም ብዙም ሳይቆይ ከቅጣት ምት ተሻጋሪ ኳስ ቸርነት ጉግሳ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ጎል እንዳይሆን ያደረገው አጋጣሚ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ጎል ለመድረሳቸው ማሳያዎች ናቸው።
ከደቂቃዎች በኋላ በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ወደ ማጥቃት ሽግግሩ ገብተው በተራቸው የቅዱስ ጊዮርጊስን የግብ ክልል መፈተሽ ጀምረዋል። በቀኝ መስመር ያደላው የማጥቃት ኃይላቸው በ10ኛው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በራሱ የጎል አቅራቢያ የሰራውን ጥፋት ሽመክት ጉግሳ ነጥቆ የመታውን የግቡ ቋሚ የመለሰበት አደገኛ የማግባት አጋጣሚ ነበር። ግለቱን ይዞ ሳያቋርጥ የቀጠለው ጨዋታ ምንም እንኳ በሁለቱም በኩል አስፈሪ የጎል ሙከራ አያደርጉ እንጂ ተመጣጣኝ ፉክክር እያሳዮን መዝለቅ ችለዋል። በ30ኛው ደቂቃም የዐፄዎቹ በፈጣን እንቅስቃሴ ከቀኝም መስመር የተነሳው ዓለምብርሀን ይግዛው በቀጥታ ባልተለመደው ግራ እግሩ በጥሩ ሁኔታ መቶ ለጥቂት የወጣበት ሙከራ ተጠቃሽ ነው።
የተጫዋቾች አላስፈላጊ ውዝግቦች እና ጉሽሚያዎች መልካም እንቅስቃሴ እያስመለከተን የቀጠለውን ጨዋታ ወደ ሌላ መንፈስ ቀይሮታል። የዕለቱም ዳኛ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ተደጋጋሚ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እንዲመዙ አድርጓቸዋል። ከቀኝ መስመር በመነሳት አደጋ ሲፈጥሩ የቆዮት ፋሲል ከነማዎች ጥረታቸው ተሳክቶ በ44ኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አግኝተዋል። በመልሶ ማጥቃት ከታፈሰ የተነሳው ኳስ ከሽመክት ጉግሳ ጋር ደርሶ ኳስ በጥሩ መንገድ ያቀበለውን ከሳጥን ውጭ በግሩም ምት ታፈሰ ሰለሞን ኳስና መረብን አገናኝቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ፈራሰኞቹ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ጨዋታው ለመግባት ጥቃት ለመሰንዘር ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም ይሄን ያህል ስልነት ይጎለው ነበር። ይህን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማጥቃት ጥለውት የሚሄዱትን ቦታ ፋሲል ከነማዎች ለመጠቀም የሚደረግ ጥረት ጨዋታውን ከፍ ወዳለ የፉክክር ስሜት ቀይሮታል። በዚህ ሂደት የቀጠለው ጨዋታ በ57ኛው ደቂቃ አስገራሚ ነገር ተከስቷል። ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በጠንካራ ምቱ የመታው ኳስ ከጎል ውጪ በተበጠሰው መረብ በመሽሎኩ ምክንያት መረቡ ጥገና እስኪደረግለት ድረስ ጊዜ መውሰዱ አንድ ትዕይት ነበር። ጨዋታው ካቆመበት ቢቀጥልም በድጋሚ በተጫዋቾች መካከል በተደጋጋሚ የሚደረግ ጉሽሚያ የዕለቱን ዳኛ ስራ ሲያከብደው ተስተውሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምንም ዓይነት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ለመፍጠር ተቸግረው ባለበት ሰዓት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል። በ75ኛው ደቂቃ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ላይ የፋሲሉ ከድር ኩሊባሊ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ የፋሲሎችን ፈተና አብዝቶታል።
በጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫቸውን ለመጠቀም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቆሙ ኳሶች ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ደካማ በመሆኑ ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በአንፃሩ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት በከፍተኛ ትኩረት ሲጫወቱ የቆዮት ፋሲል ከነማዎች በተገቢው መንገድ የቅዱስ ጊዮርጊስን እንቅስቃሴ ተቆጣጥረው የሚፈልጉትን ሦስት ነጥብ አግኝተው ጨዋታው ተጠናቋል።
የውድድር ዓመቱን በአምስተኛ ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገዱት የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በጨዋታው ጅማሬ አካባበቢ ብልጫ ወስደው ጨዋታውን ተቆጣጥረው የነበረ ቢሆንም ባልጠበቁት እና ባላሰቡት ሁኔታ በሰሩት ስህተት ጎል መቆጠሩ ጨዋታውን እንዳከበደባቸው ገልፀዋል። የመጀመርያ ሽንፈታቸው እንጂ ውድድሩ እንዳላለቀ መሸነፋቸው መጥፎ አለመሆኑን እና በቀጣይ የተሻለ ነገር ለማድረግ እንደሚቀርቡ አያይዘው ተናግረዋለው።
ወደ አሸናፊነት የተመለሱት የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ በበኩላቸው ቡድናቸው በጉዳት እየታመሰ በመሆኑ ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን አስቀድመው የጠበቁት ቢሆንም ግን ባሉን ልጆች ውጤት ይዞ ለመውጣት ተጫዋቾቹ መቶ ፐርሰት ያላቸውን አቅም እንደሰጡ ጠቁመው ለድሉ ስኬት ልጆቹ ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ሥራ የመጫወት ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረጋቸው እንደጠቀማቸው ገልፀው በማስከተል ታፈሰ ሰለሞን ከዚህም በላይ ማድረግ የሚችል ቴክኒካሊ አቅም ያለው ድንቅ ተጫዋች መሆኑን በአድናቆት ገልፀዋል።