ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ የዓመቱን ሁለተኛ ድል አሳክቷል

ባህር ዳር ከተማ በኦሴ ማውሊ እና ፉአድ ፈረጃ ሁለት ጎሎች ለገጣፎ ለገዳዲን 2-0 አሸንፏል።

ለገጣፎ ለገዳዲዎች በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ በአምስቱ ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ በሽር ደሊል ፣ ታምራት አየለ ፣ ብሩክ ብርሀኑ ፣ አማኑኤል አርቦ እና በጉዳት ከጨዋታው ውጪ በሆነው አንዋር አብዱልጀባር ምትክ ወንድወሰን ገረመው ፣ አቤል አየለ ፣ ያብቃል ፈረጃ ፣ ተፈራ አንለይ እና መሐመድ አበራን ወደ ቋሚ አሰላለፍ አካተው ሲገቡ ከድሬዳዋ ጋር ነጥብ ተጋርተው በነበሩበት ባህርዳር ከተማዎች በኩል የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ተደርጓል፡፡ ሳላአምላክ ተገኝን በመሳይ አገኘሁ ፣ ቻርለስ ሪባኑን በአብስራ ተስፋዬ እና ሀብታሙ ታደሰን በኦሴ ማውሊ ተክተዋል፡፡

ጨዋታው ገና ከጅምሩ የባለ ሜዳው ባህር ዳር ከተማ የበላይነት ጎልቶ የታየበት ነበር፡፡ መሀል ሜዳውን እና ሁለቱን የመስመር ኮሪደሮች ገና በጊዜ መጠቀም የጀመሩት የጣና ሞገደኞቹ 2ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚውን የአጋማሹን ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡ ከግቡ ትይዩ የተገኘን የቅጣት ምት ኦሴ ማውሊ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታው ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው እንደምንም ባወጣበት ጥቃት መሰንዘራቸውን ጀምረዋል፡፡ ኳስን ከኋላ ክፍላቸው መስርተው በተረጋጋ የጨዋታ ቅርፅ በተለይ በዱሬሳ እና አደም አማካኝነት በሁለቱ መስመሮች ጥቃትን መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ባህርዳሮች በአንፃሩ በቅብብል ወቅት የሚሰሩትን ስህተት ለገጣፎዎች አድፍጠው በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በተወሰነ መልኩ ትጋት ያሳዩ ነበር፡፡

ለዚህም ማሳያው 10ኛው ደቂቃ አካባቢ በቅብብል ወቅት የሰሩትን ስህተት የለገጣፎዎች አማካዮች አግኝተው ወደ ሳጥን ሲያሻግሩ አማካዩ ተፈራ አንለይ በግንባር ገጭቶ ግዙፉ የግብ ዘብ ታፔ አልዛየር የያዘበት በቡድኑ በኩል የምትጠቀሰዋ አጋጣሚ ነበረች፡፡ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ የባህርዳርን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለመቋቋም የተሳናቸው ይመስሉ የነበሩት እና ወደ ኋላ አፈግፍገው መልሶ ማጥቃትን በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት ለመጫወት ሰታትሩ የታዩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡

27ኛው ደቂቃ ላይ ሔኖክ ኢሳያስ በቀኝ የለገጣፎ የግብ አቅጣጫ ለአደም አባስ የሰጠውን በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ጎል ሲያሻማ የተከላካዮች ስህተት ታክሎበት ጋናዊው አጥቂ ኦሴ ማውሊ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የባህር ዳር ደጋፊዎችን ጮቤ አስረግጧል፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ተጋጣሚያቸው የሚሰራቸውን ስህተቶች ለመጠቀም የዳዱት ለገጣፎዎች ሁለት ሙከራን አድርገዋል፡፡ 34ኛው እና 37ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ አምበሉ አስናቀ ተስፋዬ ከቅጣት ምት ወደ ጎል መትቶ ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር የያዘባቸው የሚጠቀሱ ዕድሎቻቸው ናቸው፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃራዊ መቀዛቀዞች የታዩበት ቢሆንም ኳስን የመቆጣጠሩ ድርሻ ግን አሁንም በባህር ዳር ከተማ የቀጠለ ነበር፡፡ 54ኛው ደቂቃ ላይ ፉአድ ፈረጃ ከቅጣት ምት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው ሲመልሳት ከፊቱ የነበረው ኦሴ ማውሊ በድጋሚ ሲመታ ወንድወሰን በቀላሉ ይዞበታል፡፡ በባህር ዳር በሁሉም ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ለገጣፎ ለገዳዲዎች የተጫዋች ለውጥ አድርገው በተሻጋሪ ኳሶች ወደ ካርሎስ ዳምጠው በመጣል ለመጫወት ቢሞክሩም የተጫዋቹ ተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም የኋላ ኋላ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለ ሆኗል፡፡ 65ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዮናስ በርታ ከኋላው የነበረውን አደም አባስ ባለመመልከቱ የተነጠቀውን ኳስ አደም እየነዳ ወደ ሳጥን ገብቶ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ የሰጠውን ፉአድ ፈረጃ ወደ ጎልነት በመቀየር የጣና ሞገደኞቹን ወደ 2-0 አሸጋግሯል፡፡

ለጎሏ መቆጠር ስህተት የሰራው ዮናስ በርታ ተቀይሮ በመግባት ሜዳ ላይ 16 ደቂቃዎችን ከቆየ በኋላ በአንተነህ ናደው ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል፡፡ በተወሰነ መልኩ ሁለተኛ ጎል መረባቸው ላይ ካረፈ በኋላ መነቃቃት ይታይባቸው የነበረው ለገጣፎዎች 71ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር መሐመድ አበራ ወደ ጎል ሲያሻግር የባህር ዳሩ ተከላካይ ሔኖክ ኢሳያስ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ራሱ ላይ ለመቆጠር ኳሷ ወደ ጎል ብትንደረደርም ታፔ አልዛየር ይዟታል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎችም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከእንቅስቃሴ ባሻገር የጠሩ ዕድሎችን መመልከት ሳንችል ጨዋታው በጣና ሞገደኞቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የአሸናፊው ባህርዳር ከተማ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ውጤቱ ለደጋፊዎቻቸው መልካም መሆኑን ከተናገሩ በኋላ ድሉ ለቡድኑ በቀጣይ ከፋሲል ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው እና በራስ መተማመን በቡድኑ ውስጥ እንደሚያሳድግላቸው በሀሳባቸው ገልጸዋል፡፡ የለገጣፎ አሰልጣኝ የሆኑት ጥላሁን ተሾመ በበኩላቸው ጥሩ ጨዋታ እና ፉክክር እንደነበር ጠቁመው በማጥቃትም ሆነ በመከላከሉ ጥሩ እንደሆኑና የልምድ ማነስ እና በጨዋታው የነበረው የኮሚኒኬሽን ችግር ከትኩረት ማጣት ጋር ተደምሮ ለሽንፈት እንደዳረጋቸው እና በቀጣይ የድሬዳዋ ቆይታ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት እንደሚሰሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

ያጋሩ