በውብ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን መቻልን 2-1 ረቷል።
መቻል በአራተኛ ሳምንት ፋሲል ከነማ ከረታበት ስብስቡ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። ምንተስኖት አዳነ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ተሾመ በላቸው እና ምንይሉ ወንድሙን በየዓብስራ ሙሉጌታ ፣ በኃይሉ ግርማ ፣ እስራኤል እሸቱ እና በረከት ደስታ ሲለውጥ በአንፃሩ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ወላይታ ድቻን ካሸነፈበት ስብስቡ ሐቢብ ከማልን በሲሞን ፒተር ብቻ በመተካት የዛሬውን ጨዋታ ማድረግ ችሏል።
ፋጣን ያለ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አዝናኝነቱ የጎላ ነበር። የመጀመርያው ጎል እስከተቆጠረበት ጊዜ ድረስ ጠንከር ያለ የጎል ሙከራ በሁለቱም በኩል ባንመለከትበትም ተመጣጣኝ በሆነ እንቀስቃሴ እየታየበት መዝለቅ ችሎ ነበር። በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ መድኖች በፈጠሩት ጫና በ20ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። ከቀኝ መስመር ኪቲካ ጅማ ወደ ሳጥን ለማሻገር የላከውን ኳስ አህመድ ረሺድ ኳሱን ለማራቅ ቢያስብም ራሱ ላይ ጎል ለማስቆጠር ችሏል። አህመድ ረሺድ በያዝነው የውድድር ዓመት በራሱ ላይ ጎል ያስቆጠረ የመጀመርያው ተጫዋች አድርጎታል።
ውበቱን ጠብቆ የቀጠለው ጨዋታ የመቻሎችን አፀፋዊ ምላሽ በ28ኛው ደቂቃ በተቆጠረ ጎል አስመልክቶናል። ከማዕዘን ምት የተጣለውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በአግባቡ ከግብ ክልሉ ያላራቀውን በኃይሉ ግርማ አግኘቶት በጥሩ ሁኔታ ጎሉን አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከአቻነት ጎል መቆጠር በኋላ ምንም እንኳ በመድኖች በኩል ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም አልፎ አልፎ ወደ ጎል ለመድረስ የሚደረጉ ቅብብሎች አድርገዋል። በአንፃሩ በመቻሎች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት በተደጋጋሚ የመድኖችን የግብ ክልል ሲፈትሹ ቆይተዋል። በዚህም ፍፁም ጥላሁን ከሳጥን ውጭ መቶት አቡበከር ኑራ ካስ እና መረብ እንዳይገናኝ ወደ ውጭ ያወጣበት እንዲሁም አህመድ ረሺድ በጥሩ መንገድ ከግራ መስመር ያሻገረውን እስራኤል እሸቱ በግንባሩ በመግጨት ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ መቻሎችን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ ከጅምሮ ከፍተኛ ጫና አሳድረው መጫወታቸውን የቀጠሉት መድኖች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በዚህም ሂደት በ57ኛው ደቂቃ በድጋሚ መምራት የሚችሉበትን ጎል አግኝተዋል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በእርጋታ ኳስን መስረተው በጥሩ ቅብብሎች በመውጣት መቻል የግብ ክልል በመድረስ ከግራ መስመር ተቀይሮ የገባው ያሬድ ካሳዬ ያሻገረውን በጥሩ አጨራረስ ባሲሩ ዑመር በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎልነት በመቀየር የቡድኑን ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።
የጨዋታው የኃል ሚዛን ወደ መድኖች አድልቶ ተጨማሪ ጎሎች ለማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ሲሞክሩ ተመልክተናል። በተቃራኒው መቻሎች ከደካማው የሁለተኛው አጋማሽ እንቅስቃሴ ወጥተው ከጨዋታው ሰባ ደቂቃ በኋላ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ መነቃቃት በማሳየት የአቻነት ጎል በከንዓን ማርክነህ አማካኝነት አደገኛ ጥቃት ሰንዝረው ለጥቂት ወደ ውጭ ሊወጣበት ችሏል። በድጋሚ በ75ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ኳስ ተሻገረውን ተቀይሮ የገባው ምንይሉ ወንድሙ አግኘቶ ወደ ጎል ቢመታውም የመድኖች ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ በአስደናቂ ሁኔታ አግዶበታል።
በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ መድኖች ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከመከላከል ይልቅ ኳስን ተቆጣጥረው ብልጫ በመውሰድ ተጨማሪ ጎሎች ለማስቆጠር ያሰቡ ይመስል ነበር። በመቻሎች በኩል ግርማ ዲሳሳ አቀብሎት ግሩም ሀጎስ ወደ ጎል መቶት አቡበከር ኑራ ካዳነበት ሙከራ ውጪ ሌላ ተጠቃሽ አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን አሸናፊነት ተጠናቋል።
ባህር ዳር የአምስት ጨዋታ ቆይታቸው ከመጀመርያው ሽንፈት በኃላ ቡድናቸው ተከታታይ ድል እንዲያገኝ ያስቻሉት የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ መሆኑን ይዘውት ከመጡት ዕቅድ አንፃር እንደተሳካላቸው ተናግረው የመሐል ሜዳ ክፍል ተጫዋቾቻቸው ውጤት ከመፈለግ አንፃር እንጂ ከዚህ በላይ መልካም እንቅስቃሴ በቀጣይ እንደሚያሳዩ አያይዘው ተናግረዋል።
ሽንፈት ያስተናገዱት የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው የመጀመርያው አጋማሽ ቀድሞ ጎል ቢቆጠርባቸውም ቡድናቸው ብልጫ ወስዶ እንደነበረ እና አቻ ከሆኑ በኋላ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሚችሉበት ዕድል ቢያገኙም የመጨረሻ የሜዳ ክፍል አለመረጋጋት እና ስህተት መብዛት ሊሸነፉ እዳደረጋቸው ገልፀዋል። በተጨማሪ ከውድድሩ የተማሩት ነገር እንዳለ እና በድሬደዋ ውድድር አስተካክለው እንደሚመጡ እንዲሁም እርሳቸውም ተጫዋቾቻቸው ከጫና ለመውጣት አንድ ነጥብ ቢያገኙ የተሻለ እንደነበር ገልፀዋል።