የሊጉ የባህር ዳር ከተማ መደበኛ የአምስት የጨዋታ ሳምንታት መርሃግብር ነገ ፍፃሜውን የሚያገኝባቸው ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን በተከታዩ ፅሁፍ አሰናድተናል።

ወላይታ ድቻ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የዕለቱ የመክፈቻ መርሃግብር በሊጉ ግርጌ የሚገኙትን ወላይታ ድቻዎችን ከመሪዎቹ ለመጠጋት ከሚያልሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ያገናኛል።

ሲዳማ ቡና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ማሸነፉን ተከትሎ ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ የተንሸራተቱት ወላይታ ድቻዎች እስካሁን ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻሉት ሁለት ነጥብ ብቻ ሲሆን በዚህም ቃልኪዳን ዘላለም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ካስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ውጭ ግብ ማስቆጠር ያለመቻላቸው ጉዳይ ትኩረት የሚስብ ነው።

ለመከላከሉ አብዝቶ ትኩረት የሚሰጠው ቡድኑ የማጥቃት ጨዋታው ግን ፍፁም መሻሻልን ይሻል። በመከላከል ውስጥ ግቦች ባለማስተናገድ አንድ ነጥብ ይዞ መውጣት ቢቻልም ሊጉ አሁን ከሚገኝበት ስፍራ ለመላቀቅ እና የቡድኑን የራስ መተማመን ለማሻሻል ድሎች ወሳኝ ሚና ያላቸው ሲሆን ድቻዎችም ይህን ለማድረግ ማጥቃታቸውን ማረም የግድ ይላቸዋል። በወላይታ ድቻዎች በኩል ፂሆን መርዕድ ፣ አንተነህ ጉግሳ ፣ እንድሪስ ሰዒድ እና ቢኒያም ፍቅሬ ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

በሰንጠረዡ አናት በ7 ነጥቦች በ3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጀመሪያ ጨዋታ ከደረሰባቸው ሽንፈት ማግስት በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ባሳኳቸው አውንታዊ ውጤቶች ደረጃቸውን ማሻሻል ችለዋል።

ምንም እንኳን በመጨረሻው የአርባምንጭ ጨዋታ ፍፁም ደካማ እንቅስቃሴን ቢያደርጉም ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ የመሻሻል ምልክቶችን እያሳየ ይገኛል። በተለይም አዲስ ፈራሚያቸው አማካዩ ስቲፈን ናያርኮ የቡድኑን የመሀል ለመል ማጥቃት በማሻሻል ረገድ ጥሩ ተፅዕኖ እያሳረፈ ይገኛል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በነገው ጨዋታ ወሳኙን አማካያቸውን ሳምሶን ጥላሁን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ትልቁ ዜና ሲሆን ከእሱ በተጨማሪ አጥቂው እንዳለ ደባልቄም እንዲሁ ከጉዳት ተመልሷል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በስድስት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች በሦስት እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ቀሪው አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተደምድሟል።

ይህን ጨዋታ ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት ሲመራው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ እና ለዓለም ዋሲሁን በረዳትነት ፣ ባህሩ ተካ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ መርሃግብር 6ኛ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎችን 12ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች ጋር ያገናኛል።

ሁለት ተከታታይ ድሎችን ማሳካት የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለቱም ጨዋታዎች ሜዳ ላይ የነበራቸው እንቅስቃሴ እምብዛም አሳማኝ አልነበረም። በተለይ በመጨረሻው የሲዳማ ቡና ጨዋታ ቡድኑ በሁሉም መመዘኛዎች በተጋጣሚያቸው ከፍተኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ቢሆንም ወሳኙን ነጥብ ግን ይዘው መውጣት ችለዋል።

እንደ አዲስ እየተገባ ለሚገኘው የተመስገን ዳና ስብስብ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማስመዝገብ አለመቻላቸውን ተከትሎ የተፈጠረውን ጫና ለማለዘብ ሁለቱ ተከታታይ ድሎች በሥነ ልቦና ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይታመናል። በመሆኑም ቡድኑ አሁን ላይ ከውጤት ጎን ለጎን በጨዋታዎች ላይ ራሱን ይበልጥ ስለመግለፅ ወደ ማሰብ መምጣት ይኖርበታል።

በነገው ጨዋታ ቡናማዎቹ አማኑኤል ዮሐንስን ከጉዳት መልስ የሚያገኙ ሲሆን ሌላኛው አማካይ ሮቤል ተክለሚካኤል ግን በጉዳት የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል።

በአራት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች በአራቱም ጨዋታዎች በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ወጥ የሆነ የሜዳ ላይ ብቃትን ለማሳየት ተቸግረዋል።

የባህር ዳር ቆይታቸውን በድል ለመደምደም የሚያልሙት አርባምንጭ ከተማዎች ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በደርሶ መልስ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 የረቱባቸው ጨዋታዎች መነሻ ይሆኗቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። እርግጥ ከአምናው የተለወጠውን ኢትዮጵያ ቡናን ቢገጥሙም ነገም ከኳስ ውጪ ብዙ ደቂቃዎችን እንደሚያሳልፉ የሚጠበቁት አርባምንጮች በመልሶ ማጥቃት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጉዳት ለማድረስም እንደሚሞክሩ ይጠበቃል።

በሊጉ ነገ ኢትዮጵያ ቡናን ከሚገጥሙበት ጨዋታ አንስቶ በተከታታይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማን የሚገጥሙት አርባምንጭ ከተማዎች እነዚህን ተከታታይ ፈታኝ መርሃግብሮች እንዴት ይወጡታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል። በአርባምንጭ ከተማዎች በኩል ተከላካዩ አንድነት አዳነ አሁንም ከጉዳቱ ያልተመለሰ ሲሆን ኬንያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ ግን ለነገው ጨዋታ የስብስባቸው አካል እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ16 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች 7 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነትን ሲይዙ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ5 ጨዋታዎች የረቱ ሲሆን የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የሚመሩ ሲሆን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኤፍሬም ሀይለማሪያም በረዳትነት እንዲሁም ዮናስ ካሳሁን በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ለጨዋታው ተመድበዋል፡፡

ያጋሩ