ሪፖርት | ሀድያ ሆሳዕና የባህር ዳር ቆይታውን በድል አጠናቋል

ሀድያ ሆሳዕና በፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ወላይታ ድቻን በማነሸፍ ሦስተኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡

ሁለቱም ክለቦች ካለፈው ጨዋታቸው የአንድ አንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል፡፡ ወላይታ ድቻ በኢትዮጵያ መድን ከተሸነፈበት ሀብታሙ ንጉሴን በያሬድ ዳዊት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከአርባምንጭ ጋር ያለ ጎል ከፈፀሙበት ጨዋታ ሪችሞንድ ኦዶንጎን በራምኬል ሎክ በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል፡፡

በፌደራል አልቢትር ኤፍሬም ደበሌ መሪነት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ውጪ ወደ ጎል ደርሶ ልዩነት ለመፍጠር የተደረገበት ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ቡድኖቹ በተመሳሳይ የ4-3-3 የጨዋታ ቅርፅ አቀራረባቸውን አድርገው ሜዳ ላይ ቢታዩም የነበራቸው የጨዋታ መንገድ ግን ደካማ በመሆኑ ግልፅ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን መመልከት አልቻልንም፡፡ ከአማካዩ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን መነሻቸው ካደረጉ ኳሶች በሁለቱም መስመሮች በኩል ጥቃት ለመሰንዘር ይጥሩ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በተጋጣሚያቸው ላይ ማሳየት ቢችሉም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ግን እጅጉን ደካሞች ነበሩ፡፡

ከተደረጉ ሙከራዎች መካከል ግርማ በቀለ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ቢኒያም ገነቱ በቀላሉ የያዘበት እና 27ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከቅጣት ምት ምት አሻምቶ ብርሀኑ በቀለ በግንባር ገጭቶ ኢላማዋን መጠበቅ ካልቻለችው ሙከራ ውጪ እምብዛም በቂ የሆኑ ዕድሎችን መመልከት አልቻልንም፡፡የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያሙ ወላይታ ድቻ አብዛኛዎቹን የአጨዋወት መንገድ በተሻጋሪ እና በቆመ ኳሶች ላይ አድርጎ በመጫወት ወደ አጥቂው ስንታየው መንግሥቱ ላይ በመጣል ጎል ለማግኘት ቢታትሩም የሚሻገሩ ኳሶች ለሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ ፔፕ ሰይዶ በቀላሉ ይያዙ ስለነበር የጠሩ ዕድሎችን ለመፍጠር አላስቻላቸውም፡፡

ከዕረፍት መልስ ሀድያ ሆሳዕናዎች አንፃራዊ መሻሻሎች ማሳየት ሲችሉ ወላይታ ድቻዎች ቃልኪዳን ዘላለምን በዮናታን ኤልያስ በመለወጥ በሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ለማግኘት ቢጥሩም የሚያሻግሯቸው ኳሶችን ሊጠቀም በተደጋጋሚ ይጥር የነበረው አጥቂው ስንታየው መንግሥቱ ቶሎ ቶሎ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ውስጥ በመገኘቱ ጎል ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ይባክን ነበር፡፡

በተሻለ አጨዋወት በፈጣን የአንድ ሁለት ቅብብል ያየለ ብልጫ ያሳዩ የነበሩት ነብሮቹ ጎል እና መረብን ለማገናኘት እጅጉን በታታሪነት ተጫውተዋል፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ40 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘን የቅጣት ምት አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታው ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ባወጣበት ሙከራ ሀድያዎች ወደ ጎል መጠጋት ጀምረዋል፡፡ የማጥቃት ፍላጎታቸው እጅጉን የተቀዛቀዘው እና ኳስን በሚያገኙበትም ወቅት አጥቂዎቻቸው በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ አጨዋወትን ያዘወትሩ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በተከላካይ በተሰራ ጥፋት ግብ ሊቆጠርባቸው ግድ ብሏል፡፡

በሁሉም ረገድ ብልጫ የተወሰደበት ቡድኑ 67ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ባዬ ገዛኸኝ ላይ ሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ወደ ጎልነት ለውጧት ሀድያ ሆሳዕናን መሪ አድርጓል፡፡

ጎል ካስተናገዱ በኋላ የሀድያ ሆሳዕናን ማፈግፈልግ አስተውለው በተወሰነ መልኩ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው ለማጥቃት የዳዱት ወላይታ ድቻዎች ሁለት የጎሉ ዕድሎችን ፈጥረዋል፡፡ 78ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ አበባየው ሀጂሶ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ሞክሮ ፔፕ ሰይዶ የያዘበት እና ከመሀል ሜዳ የተሻገረን ኳስ 84ኛው ደቂቃ ስንታየው መንግሥቱ በግንባር ገጭቶ አመቻችቶለት ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ መኮንን በግራ እግሩ መቶ የግቡ የላይኛው ብረት የመለሰበት በክለቡ አስቆጪ ሙከራዎች ቢሆኑም ሀድያ ሆሳዕናዎች ተሳክቶላቸው 1-0 በማሸነፍ የባህር ዳር ቆይታን በድል አገባደዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሽንፈት የገጠመው ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በሽንፈቱ መከፋታቸውን በመግለፅ የአጨራረስ ክፍተት እና የተጫዋቾች መጎዳት ፈተና እንደሆነባቸው በጨዋታውም ማጥቃት ላይ መረጋጋት ባለመቻላቸው በተጋጣሚያቸው ተገማች ለመሆን እንደተዳረጉም ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ ድል የቀናው ሀድያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ጨዋታው ፈታኝ እንደነበር እና የጠበቁት እንደገጠማቸው ከገለፁ በኋላ ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው ውጤቱንም ይዘው ለመውጣት እንደቻሉ ሀሳባቸውን መናገር ችለዋል፡፡