ሪፖርት | ቡናማዎቹ ወደ ሰንጠረዡ አናት ፉክክር ተቀላቅለዋል

በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ኢትዮጵያ ቡና አርባምንጭ ከተማን 2-0 አሸንፏል።

ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን ከረታበት አሰላላፍ ሮቤል ተክለሚካኤል እና ጫላ ተሺታን በአማኑኤል ዮሐንስ እና መሐመድኑር ናስር በመቀየር ወደ ሜዳ ሲገባ አርባምንጭ ከተማዎች ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች በናርድ ኦቼንግ እና አሸናፊ ኤሊያስን በእዩብ በቀታ እና አሕመድ ሁሴን በመተካት ተጠቅመዋል።

የዕለቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ጨዋታው ባስጀመሩበት ቅፅበት ገና በአርባኛው ሰከንድ ነበር ፈጣን ፍፁም ቅጣት ምት ያስመለከተን። ከሄኖክ ደልቢ የተሻገረትን መሐመድኑር ናስር ኳሱ ተቆጣጥሮ ለማለፍ በሚያደርገው ጥረት የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ብሩክ በየነ ቢመታውም ሳይጠቀምበት ቀርቶ ኳሱን ወደ ላይ ሰቅሎታል። ብሩክ በዚህ የውድድር ዓመት ሁለተኛ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ ሳይጠቀም መቅረቱ አስገራሚ ሆኗል።

የጨዋታው ሂደት ቀጥሎ ቡናዎች ኳስ ተቆጣጥረው በመያዝ ወደ አርባምንጭ ሳጥን በመጠጋት ዕድሎችን ለመፍጠር ሲያስቡ በአዞዎቹ በኩል ቡናዎች ኳሱን መስርተው እንዳይወጡ በማፈን አደጋ ለመፍጠር ያለሙ እንቅስቃሴዎችን እየተመለከትን ወደ 20 ደቂቃ ተሻግሯል። በጎል ሙከራ ሳይታጀብ ተቀዛቅዞ የቀጠለውን ጨዋታ ወደ ጥሩ ፉክክር ስሜት የሚቀይር ጎል በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተቆጥሯል። በ26ኛው ደቂቃ ከኃይለሚካኤል አደፍርስ ከግራ መስመር የተላከውን ኳስ ብሩክ በየነ ዘሎ በግንባሩ በመግጨት የቡናማዎቹን የመጀመርያ ጎል አስገኝቷል።

የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያላስደሰታቸው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሦስት ተጫዋቾችን ድንገተኛ ለውጥ በማድረግ ምላሽ ለመስጠት ተጭነው መንቀሳቀስ ቢችሉም አደገኛ የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ተችገረው ታይተዋል። ቡናዎች ተረጋግተው የመጀመርያውን ጎል ባገኙበት የኳስ ቁጥጥጥሩን የመውሰድ ብልጫ ሳስቶ ቢታይም ለቡድኑ መጠነኛ ዕፎይታ የሚሰጥ ሁለተኛ ጎላቸውን በ45ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከአርባምንጭ ያቋረጡትን ኳስ ሄኖክ ደልቢ መሀል ሜዳ ላይ ብሩክ በየነ ተቀብሎ በጥሩ ሁኔታ በተከላካዮች መሀል አሳልፎለት ተቀይሮ የገባው አንተነህ ተፈራ በግራ ከጠባብ አንግል ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስም ተሻሽለው የቀረቡት አርባምጮች በተመስገን ደረሰ የግል ጥረት በጨዋታው የመጀመርያውን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢያገኙም ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አድኖበታል። አርባምንጮች ጫና ፈጥረው እየተጫወቱ ባለበት ቅፅፈት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት ጨዋታውን መቆጣጠር የሚችሉበትን ግልፅ የጎል ዕድል አግኝተው አብዱልአዚዝ ቶፊክ ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጪ ነበር።

የጨዋታው ሂደት ወደ 64ኛው ደቂቃ ደርሶ ዕረፍት አልባ የጎል ዕድሎችን በሁለቱም በኩል አሳይቶናል። ፈጣኑ አጥቂ አንተነህ ሳይጠበቅ ያገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ መቶት ለጥቂት በግቡ አናት ከወጣበት ጥቃት በኋላ በምላሹ አርባምንጮች ቡናማዎቹ ሳጥን ደርሰው እንዳልካቸው መስፍን በጥሩ ሁኔታ የመታውን ግብ ጠባቂው በረከት አማረ እንደምንም አድኖት የተፋውን ኳስ ተመስገን ደረሰ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል በረከት በድጋሚ ከወደቀበት ተነስቶ በማዳን ኢትዮጵያ ቡናን ታድጎታል።

ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዞዎቹ ጥረታቸው በጎል አለመታገዙ ተከትሎ በተጫዋቾቹ ላይ የመውረድ ስሜት መታየቱ የተለየ ነገር እንዳያሳዩ አድርጓቸዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በመልሶ ማጥቃት ጨዋታውን መግደል ከሚችሉበት እንቅስቃሴ ወጥተው በተረጋጋ ሁኔታ ኳሱን በመቆጣጠር ክፍተቶች ለማግኘት ጥሩ ቅብብሎች ቢያደርጉም የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በቀላሉ ኳሱን ይነጠቁ ነበር። በቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታው በንፅፅር ቀዝቀዝ ብሎ ቀጥሎ በሁለቱም በኩል የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከሀዘን መልስ ቡድናቸውን በመምራት ተከታታይ ድላቸውን ያሳኩት የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት አስተያየት ተጋጣሚያቸው ወደ ሜዳቸው ወርደው እንደሚመጡ በመጠበቅ በፍጥነት ጎል ማስቆጠር እንዳለባቸው ያሰቡት እንደተሳካላቸው ተናግረው ከዕረፍት መልስ ሁለቱን ጎሎች ለመቀነስ ተጭነው ሲመጡ ተጨማሪ ጎል ለማከል ቢያስቡም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ችግሮች እንደነበሩ ተናግረዋል። አክለውም ብሩክ በፍፁም ቅጣት ምት ቢስትም ቡድናቸው ዕምነት የሚጥልበት አጥቂ መሆኑና በቀጣይ ፍፁም ቅጣት ምት ይመታል የሚለውን ወደ ፊት የሚያዩት መሆኑን ገልፀዋል።

የባህር ዳር ቆይታቸውን በሽንፈት ያጠናቀቁት የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው በመጀመርያ አጋማሽ ጥሩ ባልነበሩት አጋጣሚ ጎል እንደተቆጠረባቸው ጠቅሰው ከዕረፍት መልስ ይሻሉ የነበረ ቢሆንም ጎል አለማስቆጠራቸውን እንደ ክፍተት አስቀምጠዋል። የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ስለማድረጋቸው ለባላ ጋራ ቡድን ኳሱን መስርተው እንዲወጡ መፍቀዳቸው እና የትኩረት ማጣት ለመቀየር እንደተገደዱ በመናገር በቀጣይ መከላከሉ ፣ ዕድሎችን አለመጠቀም እና የኳሶች መቆራረጦችን አስተካክለው እንደሚመጡ ጠቁመዋል።