ባሳለፍነው የውድድር ዓመት የከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገው ቡራዩ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡
በ2014 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ከአንደኛ ሊግ በማደግ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገው እና በምድብ ለ ስር ተደልድሎ በ29 ነጥቦች በምድቡ ካሉ አስር ክለቦች ሦስተኛ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀው ቡራዩ ከተማ በ2015 ሁለተኛውን የውድድር ተሳትፎ ለማድረግ ጉዞውን አዲስ አሰልጣኝ በመቅጠር ጀምሯል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ በየነም አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡
አሰልጣኝ መሳይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አሰልጣኝነትን በመጀመር በነቀምት ከተማ ፣ በኢትዮጵያ መድን ረዳት አሰልጣኝ ፣ በጅማ አባ ጅፋር ፣ ፌደራል ፖሊስ ፣ ዱከም ከተማ እና ያለፈውን ዓመት በቀድሞው ክለባቸው ቡታጅራ ከተማ በድጋሚ እስከ አጋማሹ ከቆዩ በኋላ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን በማሰልጠን ዓመቱን ያገባደዱት ሲሆን ከአሰልጣኝነት በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት የኦሮሚያ ክለቦች የቴክኒክ ኮሚቴም ሆነው ሰርተዋል።