የሊጉ የባህር ዳር ከተማ ቆይታ ነገ መቋጫውን ሲያገኝ ዐፄዎቹን ከጣና ሞገዶቹ የሚያገናኘውን ተጠባቂ ጨዋታ በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።
ለፕሪምየር ሊጉ ተጨማሪ ድምቀትን እየፈጠረ የሚገኘው ይህ መርሐግብር እጅግ ከፍ ባለ የመሸናነፍ ስሜት እና በከፍተኛ የደጋፊዎች ቁጥር ታጅቦ ይደረጋል። ካርዶች እና አነጋጋሪ የዳኝነት ውሳኔዎች የማያጡት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉ ለሰባተኛ ጊዜ ነገ 10 ሰዓት ላይ ሲል በባህር ዳር ስታዲየም ጅማሮውን ያደርጋል።
ሁለቱም ቡድኖች አማካይ የሚባል የውድድር ዘመን አጀማመር እያደረጉ ይገኛሉ። ፋሲል ከነማዎች እስካሁን በሊጉ ሦስት ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን በሁለቱ ድል ሲያረጉ በቀሪው አንድ ጨዋታ ሽንፈትን በማስተናገድ በስድስት ነጥቦች በስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ፋሲል አዳማ ከተማን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በረታባቸው ጨዋታዎች ሜዳ ለይ የተሻለ ጊዜን ቢያሳልፍም በመቻል በተረቱበት ጨዋታ ግን ፍፁም ደካማ ነበሩ። በአንፃሩ አራት ጨዋታዎችን ማድረግ የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች በሁለት ጨዋታዎች ሲረቱ በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አንድ ሽንፈት እና የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በሰባት ነጥቦች አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ከነገው ወሳኝ ፍልሚያ አስቀድሞ ሁለቱም ቡድኖች በተለያየ መንገድ እጅግ ወሳኝ የሚባል ድልን አሳክተው የመምጣታቸው ጉዳይ ጨዋታው በተሻለ የፉክክር ስሜት እንዲደረግ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ያለ ሁለቱ ቁልፍ አማካዮቻቸው (ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮ) እንደመጫወታቸው ይቸገራሉ ተብሎ ቢገመቱም ከአስደናቂ የሜዳ ላይ ትጋት ጋር ወሳኙን ድል ሲያሳኩ በተመሳሳይ የአደራደር እና የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ለገጣፎን የገጠሙት ባህር ዳር ከተማዎች በተመሳሳይ ባለድል መሆን ችለዋል።
ፋሲል ከነማዎች በጊዮርጊሱ ጨዋታ በተለይ ከኳስ ውጭ የነበራቸው አቀራረብ ትኩረት የሚስብ ነበር። በተለመደው 4-1-4-1 ቅርፅ በአምስት ተጫዋቾች ወደ ላይ ተጠግተው ጫና ለማሳደር የሞከሩት ዐፄዎቹ ከጀርባ የሚደረጉ ሩጫዎችን ለመከላከል የተከላካይ መስመራቸውን በጥንቃቄ ወደ በመካከለኛ አቋቋም እንዲጀምሩ ያደረጉ ሲሆን በአደረጃጀታቸው መሀል የሚገኙ የተጋጣሚ ተጫዋቾችን እንቅስቃሴ እየተከታተለ በማቋረጥ ረገድ በተለይ ከተከላካዮቹ ፊት የነበረው ይሁን እንደሻው እንዲሁም በአጋጣሚዎች ደግሞ በመስመር ተከላካዮች ጭምር ለመከላከል ያደረጉት ጥረት አጅግ አስደናቂ ነበር።
በተለይ ታታሪ ስለመሆኑ የማይወሳለት ታፈሰ ሰለሞን በጨዋታው ያሳየው የነበረው እንቅስቃሴ እጅግ አስደናቂ ነበር። በጨዋታው ታፈሰ ሰለሞን እጅግ ወሳኟን ግብ ከማስቆጠሩ ባለፈ ከኳስ ውጭ የነበረው ትጋት እጅግ አስደናቂ ነበር። በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከቅጣት የተመለሰው የመስመር አማካዩ ሽመክት ጉግሳ ለዐፄዎቹ ሁለተንተናዊ አጨዋወት ምን ያህል ቁልፍ እንደሆነ በሚገባ አሳይቷል። ሽመክት የሚገኝበት የፋሲሎች ቀኝ መስመር ማጥቃት ነገም ለባህር ዳሮች ስጋት እንደሚደቅን ይጠበቃል።
በማጥቃቱ ከመስመር እየተነሳ ኳሶችን ወደ ሳጥን በማሻማት እንዲሁም በግሉ ፍጥነቱን በመጠቀም ተጫዋቾችን እየቀነሰ በመግባት ለማጥቃቱ ተጨማሪ አቅም የሚመሰጠው ሽመክት በመከላከሉም በሜዳው የላይኛው ክፍል ያለመታከት ጫናዎችን በማሳደር ሆነ ወደ ሜዳቸው በሚገፉባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ ለመስመር ከተላካዮቹ በቂ ሽፋን የመስጠቱ ጉዳይ እንደ ባህር ዳር ዓይነት በመስመሮች ለማጥቃት ከሚሞክር ቡድን ጋር እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ተከትሎ በነገውም ጨዋታ ሽመክት ጉግሳ በፋሲሎች በኩል በሁለቱም የሜዳው ፅንፎች የሚጠበቀው ተጫዋች ነው።
በጣናዎቹ ሞገዶች በኩል በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ በማለም ከተከላካዮች ፊት በሁለት ስድስት ቁጥሮች መጫወትን ምርጫቸው አድርገው የነበሩት አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ይህ ምርጫቸው ቡድኑ በማጥቃት ወቅት በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር እንዲኖረው ያስገደደ ሲሆን በእነዚሁ ሦስት ጨዋታዎችም የቡድኑ ማጥቃትም በመስመሮች ብቻ እንዲገደብ ያስገደደ ነበር።
የተጋጣሚያቸው ለገጣፎ ለገዳዲ የጥራት ደረጃ እንዳለ ሆኖ በለገጣፎው ጨዋታ ግን አሰልጣኙ ተጨማሪ የማጥቃት ባህሪ ያለው አማካይ በማስገባት የአደራደር ለውጥ ባደረጉበት ጨዋታ ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ከመስመሮች ባለፈ በተወሰነ መልኩ መሀል ለመሀልም ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲጥሩ ተመልክተናል። እርግጥ ‘ከፋሲል ከነማ ጋር ይህን ምርጫ ይደግሙታል ?’ የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ቡድኑ ግን በተለይ በማጥቃት ጨዋታ ወቅት የነበራቸው ተለዋዋጭነት አሰልጣኙ ይህንን አማራጭ በቀጣይ ይበልጥ ሊጠቁመበት እንደሚችሉ ግን ይታመናል።
አሁንም ቢሆን ዕድሎችን ለመፍጠር ሆነ ግቦችን ለማግኘት በመስመር ተጫዋቾቻቸው አብዝተው የሚተማመኑት ባህር ዳር ከተማዎች በነገው ጨዋታ ውጤት ይዘው የሚወጡ ከሆነ በሁለቱ መስመሮች የሚሰለፉ ተጫዋቾች ዓይነተኛ ሚናን ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመከላከሉ ረገድ በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች በጉዳት ያልነበሩት እና ከድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ አንስቶ በጣምራ በቡድን የመሀል ተከላካይ ስፍራ እየተጫወቱ የሚገኙት ፈቱዲን ጀማል እና ያሬድ ባየህ ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ይበልጥ እርጋታን እንዲላበስ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከመከላከሉ ባለፈ ሁለቱም ተጫዋቾች ከኳስ ጋር ይበልጥ የተመቹ መሆናቸውን ተከትሎ ለጣና ሞገዶቹ የኳስ ምስረታም እንዲሁ ይበልጥ እንዲሻሻል በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በአማራ ጣና ባንክ ዋንጫ በተለይ ሙሉ ዘጠና ደቂቃን ለመጫወት ፍፁም ተቸግሮ የነበረው ቡድኑ በአካላዊ መዘዘኛዎችም እንዲሁ እየተሻሻለ ይገኛል። ባህር ዳሮች በተለይም እስካሁን በሊጉ ካስቆጠሯቸው አምስት ግቦች አራቱ በሁለተኛው አጋማሽ የተገኙ መሆናቸው በዚህ ረገድ ቡድኑ ስለመሻሻሉ አይነተኛ ማሳያ ነው። በሊጉ እስካሁን ከገጠሟቸው ተጋጣሚዎች አንፃር የላቀውን ተጋጣሚ ነገ የሚገጥሙት ባህር ዳር ከተማዎች የነገውን ፈተና እንዴት ይወጣሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
ዐፄዎቹ ወሳኙ አማካያቸውን ሱራፌል ዳኛቸውን ግልጋሎት አሁንም ለቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት በጉዳት ምክንያት የማያገኙ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደው ይሁን እንዳሻውም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጥሯል። ከዚህ ባለፈም በመጨረሻው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የተሰናበተው ከድር ኩሊባሊ የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ሲሆን በአንፃሩ ተከላካዩ መናፍ ዐወል ግን ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።
በጣና ሞገዶቹ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበተውን ተከላካያቸው ተስፋዬ ታምራትን ከጉዳት መልስ የሚያገኙ ሲሆን ፍፁም ጥላሁን እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ግን አሁንም ከስብስቡ ውጪ ሲሆኑ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።
በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ ዕርከን የአጭር ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለስድስት ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች በሁለቱ ግንኙነቶች በማሸነፍ የበላይነት ያላቸው ሲሆን የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።
ይህን ተጠባቂ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የሚመሩት ሲሆን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት በረዳትነት እንዲሁም ተካልኝ ለማ ደግሞ ለጨዋታው በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኬ
ዓለምብርሀን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – መናፍ ዓወል – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – ታፈሰ ሰለሞን – በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
ፍቃዱ ዓለሙ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ቴፔ አላዛር
መሳይ አገኘሁ – ፈቱዲን ጀማል – ያሬድ ባየህ – ሄኖክ ኢሳያስ
ፈዓድ ፈረጃ – በረከት ጥጋቡ – የዓብስራ ተስፋዬ
ዱሬሳ ሹቢሳ – ኦሲ ማውሊ – አደም አባስ