ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተከናወነው የፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ ተስተካካይ ጨዋታ 0-0 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ባህር ዳር ከተማ ከለገጣፎው ጨዋታ አንፃር በሦስት የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ላይ ለውጥ አድርጓል፡፡ መሳይ አገኘሁ ፣ የአብስራ ተስፋዬ እና ኦሴ ማውሊን በሣላአምላክ ተገኝ ፣ ቻርለስ ሪቫኑ እና ፋሲል አስማማውን ሲተኩ በተመሳሳይ ፋሲል ከነማዎችም ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ሦስት ቅያሪ አድርገዋል፡፡ በቅጣት በሌለው ከድር ኩሊባሊ ምትክ መናፍ ዐወልን ፣ በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በበዛብህ መለዮን ፣ በፍቃዱ ዓለሙ ጋይራ ጆፍን በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል፡፡

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የፊፋ የቴልኒክ ኤክስፐርት ሆነው በመመረጣቸው የባህር ዳር ከተማ እና የክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ያዘጋጁለትን የካባ እና የእናመሰግንሀለን ምስሎች የእውቅና ስጦታ የዕለቱ የክብር እንግዶች በተገኙበት ከከተማው ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ እጅ ተቀብለዋል።

በበርካታ ደጋፊዎች መሀል የተከናወነው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አርባ አምስት ባህር ዳር ከተማዎች ብልጫ ያሳዩበት ነበር፡፡ ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳስ ላይ በይበልጥ ወደ መስመር ባደላ አጨዋወት ለመጫወት ሲጥሩ የታዩት የጣና ሞገዶቹ አንፃራዊ የበላይነትን ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ጋር ማድረግ ሲችሉ ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው በአንድ ሁለት ቅብብል በተለይ የበዛብህ እና ታፈሰን ጥምረት ተጠቅመው መንቀሳቀስን ቢያልሙም የባህር ዳርን የተከላካይ መስመር አልፈው ጎል ለማስቆጠር ግን እጅጉን ከብዷቸው ተመልክተናል፡፡

2ኛው ደቂቃ ላይ ሔኖክ ኢሳያስ አደም አባስ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል እንደምንም ባወጣበት አጋጣሚ ጥቃት መሰንዘር ገና በጊዜ የጀመሩት ባህር ዳሮች ይህንን ሂደታቸውን በማስቀጠል ጫናዎችን ማሳደር ችለዋል፡፡ 16ኛው ደቂቃ ላይም ፈቱዲን ጀማል ከፋሲል ተጫዋቾች የተቋረጠን ኳስ በረጅሙ በቀኝ የግብ አቅጣጫ ሲጥልለት ፈጣኑ ዱሬሳ ሹቢሳ ወደ ሳጥን ገፍቶ በመግባት ሲመታው ማሊያዊው ግብ ጠባቂ ሳማኪ ሚካኤል አሁንም በንቃት ኳሷን አስጥሎታል፡፡

የባህር ዳር ከተማን ጥቃት በአግባቡ ለመወጣት የተቸገሩት ፋሲሎች በአስቻለው ታመነ የትጋት መከላከል እና የግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል አስደናቂ ብቃት አግዟቸው ግባቸው እንዳይደፈር ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ የፋሲልን በር ከማንኳኳት ወደ ኋላ ማለትን ያልመረጡት ባህርዳር ከተማዎች 21ኛው ደቂቃ በድጋሚ ፉዓድ ፈረጃ ላይ በፋሲል የግብ ክልል አካባቢ ከግቡ ትይዩ አስቻለው ታመነ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ሳላአምላክ ተገኝ በቀጥታ አክርሮ ወደ ግብ ሲመታ የሳማኪ ሚካኤል ድንቅ ብቃት አሁንም ታክሎበት ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡

ባህር ዳሮች ሁለት ሙከራን በሔኖክ ኢሳያስ እና ፉአድ ፈረጃ አማካኝነት አድርገው ሳማኪ ሚካኤል በድንቅ አቅም ጎል ከመሆን ካደነ በኋላ ጥቃትን ለማስተናገድ ቶሎ ቶሎ የተገደዱት ፋሲሎች ከ35ኛው ደቂቃ በኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት በመግባት በሀብታሙ ገዛኸኝ እና ጋይራ ጆፍ አማካኝነት ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ለግብ ጠባቂው ቴፔ አልዛየር ፈታኝ ባለመሆናቸው በቀላሉ ይዟቸዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ ተመጣጣኝ ፉክክር ነገር ግን ብዙ የማጥቃት ፍላጎትን ያስተዋልንበት አልነበረም፡፡ የሚባክኑ ኳሶችን በበረከቱበት እና ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ብዙም የጠሩ አጋጣሚዎችን ያላሳየው ሁለተኛው አርባ አምስት ፋሲል ከነማን ወደ ጨዋታ ሂደት በደንብ የመለሰም ነበር፡፡ ሜዳ ላይ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እና ጉሽሚያዎች በዘለለ የግብ ዕድሎችን ለማየት በተቸገርንበት ሲሆን አንፃራዊ የሙከራ ብልጫን ፋሲሎች ማድረግ ችለዋል፡፡ ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ አፄዎቹ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በሀብታሙ ገዛኸኝ ፣ ፍቃዱ ዓለሙን በጋይራ ጆፍ ከተኩ በኋላ በይበልጥ የፍቃዱ መግባት ያነቃቃቸው መስሏል፡፡

66ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሽመክት ጉግሳ የሰጠውን ናትናኤል ሞክሮ ታፔ ይዞበታል፡፡ 69ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ ያሬድ ባዬ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ታመነ ቢመታውም ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ ወጥታለች፡፡

ባህርዳሮች በይበልጥ በዱሬሳ አማካኝነት ጎል ለማግኘት ወደ መስመር አጋድለው ቢጫወቱም ከዕረፍት መልስ በተሻሻለ መልኩ የተንቀሳቀሱት ፋሲሎች በንቃት ማጥቃቱ ላይ ሳይቦዝኑ ተሳትፎን አድርገዋል፡፡ በሌላ የቡድኑ አስቆጪ ሙከራ መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ላይ ታፈሰ ሰለሞን ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ የመታውን ኳስ ታፔ አልዛየር ያዳነበት ምናልባት ቡድኑን ቀዳሚ ልታደርግ ብትቃረብም ጨዋታው በመጨረሻም ኳስ እና መረብ ተገናኝተው ሳያስመለክተን 0-0 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አድርጓል፡፡

የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ከጨዋታው በኋላ የደርቢ ጨዋታዎች ብዙ ጊዜ ጭንቅ እንደሆነ እና ብዙ ጊዜም በአቻ ውጤት የሚጠናቀቁ እንደሆኑ ከተናገሩ በኋላ ለማሸነፍ እንደመጡ እና ያገኙትንም የፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር አለመቻላቸው ውጤት ይዘው እንዳይወጡ እንዳገዳቸው ከገለፁ በኋላ በቡድኑ ውስጥ ያለው የተጫዋቾች ጉዳትም ዕክል እንደሆነባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በአንፃሩ የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው የደርቢ ጨዋታ ሜዳ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖን ከገለፁ በኋላ በሜዳ ላይ የነበረው ድባብ አስደሳች እንደሆነ እና ከዕረፍት በፊት እንደነበራቸው ብልጫ ተጫዋቾቻቸው ከመጓጓት አኳያ ግብ ማስቆጠር እያለባቸው ያን ማድረግ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡