በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ስር የሚደረገው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ በዘመነ መልኩ የተለያዩ መስፈርቶች ወጥተውለት እንደሚደረግ ተሰምቷል፡፡
የኢትዮጵያ እግር እግኳስ ፌድሬሽን በዚህ ዓመት ለማድረግ ካሰባቸው ስራዎች መካከል የከፍተኛ ሊግ ውድድርን በዘመነ መልኩ ማካሄድ የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ውድድሩ ዘንድሮ ከሦስቱ ምድቦች በድምሩ አስራ አምስት ክለቦች ወደ አንደኛው ሊግ የሚወርዱ ሲሆን ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ደግሞ በሁለት ምድብ ተከፍሎ የውድድሩን ጥራት ከፍ በማድረግ ለማከናወን መታሰቡንም ከቀናት በፊት መሰማቱ ይታወሳል፡፡ ቀጥታ የኦንላይን ስርጭትን የሚያገኘው ይህ ውድድር ከፊፋ ፕላስ ጋር በመቀናጀት ሽፋኑ እንደሚሰጥም ጭምር መታቀዱ ይታወቃል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችሁ መረጃ መሠረት ከሆነ ውድድሩ በፊፋ ፕላስ አማካኝነት በሆላንዱ ኢለቨን ሰቨን በተሰኘ ካምፓኒ አማካኝነት ስርጭቱ የሚተላለፍ ሲሆን ለስርጭቱም ጥራት ያለው ሜዳ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፌድሬሽኑ ሦስት ሜዳዎችን እንደለየ ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ለዚህም የሆሳዕናው አቢዩ ኤርሳሞ ስታዲየም ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ እና የባህር ዳር ስታዲየም ውድድሩ እንዲካሄድባቸው ሲወሰን አንድ ተጨማሪ ሜዳንም ለማካተት የጥራት ጉዳይ እየታየ እንዳለም ጭምር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
እንደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዲኤስቲቪ ስርጭት ሁሉ የከፍተኛ ሊግ ክለቦችም ቀደም ብለው ለቀጥታ ስርጭቱ እንዲመች የክለባቸውን ታሪክ በአግባቡ ሰድረው ማቅረብ እንዳለባቸው እንዲሁም ደግሞ ከትጥቅ አጠቃቀም ማለትም የመለያ ፣ ቁምጣ እና የካሶቶኒ አጠቃቀማቸው ሳይዘበራረቅ ወጥነት ያለው ተመሳሳይ ይዘትን የተላበሰ ሆኖ ለውድድሩ መቅረብ እንደሚገባቸውም በግልፅ በመመሪያ መልክ ለክለቦች ተቀምጦላቸዋል፡፡ በተለይ ክለቦች ወጥነት ያለውን ትጥቅን መጠቀማቸው ከማርኬቲንግ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በገቢ ራሳቸው ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ በጥብቅ ትኩረት እንዲሰጡትም ስለ መገለፁ ሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ደርሷታል፡፡