ከተጠናቀቀው ዓመት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን የወረደው አዲስ አበባ ከተማ 15 አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሦስት ነባሮችን ውል አድሷል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በ2014 የውድድር ዘመን ሲወዳደር ከቆየ በኋላ በመጨረሻው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ ሽንፈት በማስተናገዱ በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ላይ ተቀምጦ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ታችኛው የሀገሪቱ የሊግ ዕርከን መውረዱ ይታወሳል። ዘንድሮ ደግሞ የመዲናይቱ ክለብ ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር ለቀጣዩ አንድ ዓመት ለመቀጠል ከወሰነ በኋላ አስራ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የሦስት ነባሮችን ኮንትራት አድሶ በሀዋሳ ከተማ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡
ፈራሚዎቹን ስንመለከት ሳምሶን አሰፋን በቀዳሚነት እናገኛለን ፤ ግብ ጠባቂው ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና የተጠናቀቀውን ዓመት በአርባምንጭ ከተማ ያሳለፈው ሳምሶን በድጋሚ ከከፍተኛ ሊጉ ወዳሳደገው አዲስ አበባ አምርቷል፡፡ ግብ ጠባቂ ሙሴ ገብረኪዳን የክለቡ ሌላኛው ግብ ጠባቂ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ግብ ጠባቂ ከመከላከያ ጋር ከተለያየ በኋላ ማረፊያው አዲስ አበባ ሆኗል፡፡ የመስመር አጥቂው ኤርሚያስ ኃይሉም ሌላኛው ፈራሚ ነው፡፡ በፋሲል ከነማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና ባለፈው ዓመት በቀድሞው አጠራሩ መከላከያ ተጫውቶ ወደ አዲስ አበባ አምርቷል፡፡
አብርሃም ታምራት ሌላኛው አዲሱ ፈራሚ ነው፡፡ በደቡብ ፖሊስ ፣ ደደቢት እና አምና በወልቂጤ ያሳለፈው የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ የቀድሞው አሰልጣኙ ጥሪን ተከትሎ ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡ ወንድሜነህ ዘሪሁንም አዲሱ የክለቡ ተጫዋች ሆኗል፡፡ በመከላከያ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ አዳማ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን አማካይ ቡድኑን መቀላቀል የቻለው ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩ ሌላኛው ፈራሚ ነው፡፡ ከአዳማ የተገኘው እና በባህር ዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡናም የመጫወት ዕድል የነበረው ተጫዋቹ ወደ መዲናይቱ ያመራ ስድስተኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡
ወደ ክለቡ በድጋሚ የተመለሰውን የቀድሞው የድሬዳዋ እና የሀምበሪቾ አጥቂ ዘርአይ ገብረስላሴን ጨምሮ ፣ ፍቃዱ ወርቁ አጥቂ ከመከላከያ ፣ ታሪኩ ሬጀሌ ከጅማ አጥቂ አባ ቡና ፣ ሙሉቀን ተስፋዬ አጥቂ ከጌዲኦ ዲላ ፣ ከበደ አሰፋ ተከላካይ ከአቃቂ ፣ ኤፍሬም ጌታቸው ተከላካይ ከየካ ፣ መልሰው መኮንን አማካይ ከጌዲኦ ዲላ ፣ ዳዊት ደግአረገ አማካይ ከባቱ እና ይሁን ገላጋይ ግብ ጠባቂ ከጌዲኦ ዲላ አዲሶቹ ቀሪ የአዲስ አበባ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ክለቡ የሮቤል ግርማ ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ዘሪሁን አንሼቦን ውልም ለተጨማሪ ዓመት ማራዘሙን ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡