የ2015 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን በአንድ ሳምንት ሲራዘም የሚካሄድባቸው ከተሞችም ተለይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ከሚደረጉ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው አንደኛ ሊግ የ2015 ውድድር የሚጀመርበት ቀን ቀደም ብሎ የታወቀ ቢሆንም ክለቦች ከክፍያ እና ከዝግጅት ጊዜ መጥበብ ጋር በተያያዘ ባቀረቡት የይራዘምልን ጥያቄ ስለመራዘሙ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ኅዳር 3 እንደሚጀመር ተገልፆ የነበረው ውድድሩ ቀደም ብለን በገለፅነው ምክንያት ወደ ኅዳር 10 መሸጋገሩን አረጋግጠናል፡፡
ወደ 55 የሚጠጉ ክለቦችን በአምስት ምድቦች ከፍሎ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ውድድር የመጀመሪያው ዙር ውድድሮች የሚከወኑበት አምስት ከተሞችም ተለይተው ታውቀዋል፡፡ በዚህም ሀዋሳ ፣ ወላይታ ሶዶ ፣ ደብረማርቆስ ፣ አሰላ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ለማስተናገድ መመረጣቸውንም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ የምድብ ድልድሉ እና የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩ ደግሞ ጥቅምት 29 እንደሚከወን ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል፡፡