ከፍተኛ ሊግ | ደሴ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል

ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ውድድር ለመመለስ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ደሴ ከተማ የአሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ ደሴ ከተማ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በ2014 የሊጉ ውድድር ላይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት መሳተፍ ያልቻለው ክለቡ በዘንድሮው ዓመት የ2015 የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ በጠንካራ ተሳታፊነቱ በድጋሚ ለመቀጠል በማለም አስቀድሞ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥርን በዛሬው ዕለት በይፋ ፈፅሟል፡፡

አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ የክለቡ አዲሱ አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡ የቀድሞው የሼር ኢትዮጵያ ፣ አዳማ ከተማ ፣ አክሱም ከተማ ፣ ስሑል ሽረ እና ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ለቀጣዮ አንድ ዓመት ደግሞ ደሴ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ሀላፊነትን ስለ መረከባቸው ክለቡ ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቋል፡፡