በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር ከ Ethiopian Resuscitation training center ጋር አንድ ላይ በመተባበር በየክለቦቹ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ሥልጠናን ሰጥተዋል፡፡ ይህ ሥልጠና ምን ይመሰል እንደነበር የሊግ ካምፓኒው የህክምና ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆኑትን ዶ/ር ፍሬው አስራትን በማናገር ለመረዳት ችለናል፡፡
እንደ ዶ/ር ፍሬው ገለፃ ሥልጠናው በዋነኝነት ትኩረቱን ያደረገው በሜዳ ላይ የሚከሰቱ ድንገተኛ ጉዳቶችን መለየት እና ማከም የሚቻልበትን መንገድ የተመለከተ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከልብ ህመም ጋር የተያያዙ ችግሮች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ Sudden Cardiac Arrest መከሰት እና አለመከሰቱን ከመለየት በተጨማሪ ተጫዋቾች ራሳቸውን መሳት አለመሳታቸውን መለየት እና ያንን ተከትሎም መደረግ ስላለባቸው የህክምና ሂደቶች በተግባር የተደገፈ ሥልጠና መሰጠት ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከዓለምአቀፉ የአበረታች መድሃኒቶች ቁጥጥር ባለስልጣን ወይንም WADA የሚቀርቡ የተከለከሉ የመድሃኒት ዝርዝሮች በባለሙያዎች ዘንድ እንዲታወቁ በማድረግ እና ተጫዋቾችም ባለማወቅም ሆነ በቸልተኝነት እነዚህን ንጥረ ነገሮች እንዳይወሱድ ለማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ይህም የመድሃኒቶች ዝርዝር በየጊዜው የሚሻሻል እና የሚገመገም እንደሚሆንም ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፕሪሚየር ሊጉ ለሚሳተፉ ክለቦች የጉዳቶችን ዝርዝር የሚመዘግቡበት ፎርም የተዘጋጀ ሲሆን ይህንን በመጠቀም በቀላሉ የትኞቹ ተጫዋቾች ምን ጉዳት እንዳጋጠማቸው ፣ ለምን ያህል ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቁና ምን ዓይነት ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ለማወቅ ይቻላል፡፡
በሊጉ እያጋጠሙ ካሉ ጉዳቶች መካከል የጡንቻ መሰንጠቅ (muscle tear) ዋንኛው መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ገልጸዋል፡፡
የህክምና ሂደቱ በተቀላጠፈ መንገድ መሄድ እንዲችል በአማርኛ የተጻፈ ግልጽ የመመሪያ መጽሃፍም እየተዘጋጀ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ደግሞ የጤና ባለሙያዎቹ ስታንዳርዱን እንደዚሁም ጊዜውን በጠበቀ እና ትክክለኛ በሆነ መንገድ የህክምና አገልግሎትን መስጠት እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡
እንደክፍተት ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል ግንባር ቀደሙ የፊፋን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟላ FIFA Medical bag ማግኘት አለመቻል ነው፡፡ በተለይም ድንገተኛ የሆነ የልብ ህመም በሚያጋጥምበት ወቅት ለእርዳታ የሚጠቀሙበት Automated External Defibrillator (AED) የተሰኘው ማሽን እንደልብ እንደማይገኝ ተብራርቷል፡፡ ፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒው በተጠባባቂ ወንበር ላይ አንድ የክለብ ሀኪም እና ሁለት ፊዝዮቴራፒስቶች እንዲቀመጡ እና በተፈለጉበት ወቅት ግልጋሎትን እንዲሰጡ እያደረጉ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ነግረውናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች እና የሥነ ልቦና አማካሪዎች በሁሉም ክለብ እንዲኖሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፖርት አመራሮች በኩል ለተጫዋቾች ጤና እየተሰጠ ያለው ትኩረት እጅጉን የሚበረታታ ሲሆን አሁንም የተጫዋቾችን ደህንነት ከማረጋገጥ አንፃር ብዙ የቤት ስራ የሚጠበቅ ሲሆን የተጀመረውን ጥሩ አካሄድ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዶ/ር ፍሬው ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል።