ፋሲል ከነማ ከአጥቂው ጋር ተለያይቷል

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ዐፄዎቹን ተቀላቅሎ የነበረው ጋምቢያዊው አጥቂ ከክለቡ ጋር መለያየቱ ታውቋል።

ለአህጉራዊ እና ሀገራዊ ውድድሮች በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ራሱን ለማጠናከር ሲንቀሳቀስ የነበረው ፋሲል ከነማ ጋምቢያዊውን አጥቂ ጋይራ ጁፍ አስፈርሞ እንደነበር አይዘነጋም። ተጫዋቹም በሊጉ ከ116 ደቂቃዎች በላይ ግልጋሎት ሳይሰጥ የቆየ ሲሆን ክለቡ በይፋዊ ገፁ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው ዘገባ ተጫዋቹ በስምምነት እንዲለቅ መደረጉን ያመላክታል።

አብዛኛዎቹን የእግር ኳስ ህይወቱን በእስራኤሎቹ ቤን ይሁዳ ፣ ራማት ሀሻሮን ፣ ሀፓል ቤንሎድ እና ሀማ አልፋሀም በተባሉ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው እና በጆርጂያ ኤፍ ሲ ዲላ እንዲሁም ለሀገሩ ጋምቢያ ክለብ ዋሊዳን ሲጫወት ቆይቶ በክረምት ወር ፋሲልን በአንድ ዓመት ተቀላቅሎ የነበረው ይህ ተጫዋች ‘ክለቡን በአግባቡ እየጠቀመ ባለመሆኑ፣ በልምምድ እና በጨዋታ ሜዳ ላይ ደካማ አቋም በማሳየቱ’ በሚል ከክለቡ ጋር በዛሬው ዕለት ቀሪ የስምንት ወራት ውል እየቀረው በስምምነት ተለያይቷል፡፡