በሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውድድር በመጀመሪያ ጨዋታው ታንዛኒያን የገጠመው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለት ጊዜ ቢመራም ጨዋታውን በ2-2 ውጤት ጨርሷል።
በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በማድረግ እና ዕድሎችን በመፍጠር የተሻሉ የነበሩት ታንዛኒያዎች ነበሩ። የእንቅስቃሴ ብልጫቸው ፍሬ አፍርቶም 21ኛው ደቂቃ ላይ ዲክሰን ቫላንቲኖ ባስቆጠራት ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ሆኖም የታንዛኒያዎች መሪነት ለ10 ደቂቃዎች ብቻ የዘለቀ ነበር። 31ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አባቴ ያቀበለውን ድንቅ ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል።
ጨዋታው ከዕረፍት ተመልሶ አራት ደቂቃዎች እንዳለፉ ከቅጣት ምት በተነሳ እና አቱማኒ ማካንቦ በግንባሩ ባስቆጠረው ኳስ ታንዛኒያዊያኑ በድጋሚ መምራት ችለዋል። ቡድኑ መሪነቱን የሚያሰፋበት የፍፁም ቅጣት ምት ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀም ቀርቷል። ከዚህ ውጪ 80ኛው ደቂቃ ላይ የታንዛኒያው ግብ ጠባቂ ባስተናገደው ጉዳት ከአራት ደቂቃ በላይ የህክምና ዕርዳታ ሲደረግለት ቆይቷል። በዚህ ክስተት ምክንያት ሰባት ያህል ተጨማሪ ደቂቃዎች በተስተናገዱበት ጨዋታ 87ኛው ደቂቃ ላይ ከተጠባባቂ ወንበር የተነሳው ከድር ዓሊ ኢትዮጵያን አቻ የምታደርግ ወሳኝ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው በጭማሪዎቹ ደቂቃዎች ሌላ ግብ ሳያስተናግድ 2-2 ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሦስት ሀገራት በተደለደሉበት ምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን በመጪው ቅዳሜ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል።