የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ የሚያደርገውን ቆይታ የሚያስጀምሩ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ባህር ዳር ከተማ

የውድድር ዓመቱን በአስከፊ ሽንፈት ጀምሮ ወዲያው በማገገም ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከሊጉ መሪ እኩል ነጥብ የሰበሰበው ኢትዮጵያ መድን ያለፉትን አምስት የጨዋታ ሳምንታት በመቀመጫ ከተማው ሲጫወት ከነበረው ባህር ዳር ከተማ ጋር የሚያደርገው የዘንድሮ የድሬዳዋ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታ ቀልብን እንደሚስብ መናገር ይቻላል።

አዲስ አዳጊው መድን ከአሰቃቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ የ7ለ1 ሽንፈት በኋላ ከጨዋታ ጨዋታ በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ረገድ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት 7 አግብቶበት ከነበረው ጊዮርጊስ ጋር በነጥብ ተስተካክሎ የባህር ዳር ቆይታውን ቋጭቷል። በተለይ በመከላከሉ ረገድ ክፍተቶች ሲታዩበት የነበረ ሲሆን በቡድናዊ መዋቅር ይህንን የኋላ ሽንቁር በማስተካከል የማጥቃት ኃይሉን ያደራጀበት መንገድ ለተጋጣሚ ፈታኝ ቡድን አድርጎታል። በኪቲካ ጅማ እና ብሩክ ሙሉጌታ ጥምረት ሲዘወር የነበረው የፊት ኃይልም በዩጋንዳዊው አጥቂ ፒተር ሲሞን መታገዝ ሲጀምር የአማካይ መስመሩም ብርታት ቡድኑ በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል። ነገም የተከታታይ ጨዋታዎቹን ድል ወደ 5 ከፍ ለማድረግ እንደሚጥር ይታሰባል።

በደጋፊዎቹ ፊት በመጫወት የውድድር ዓመቱን የጀመረው ባህር ዳር ከተማ ከነገው ተጋጣሚው እና የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የአራት ነጥብ ልዩነት አጥቦ በላይኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ፉክክር ለመገኘት የሚያደርገው ትግል ነገ ይጠበቃል። የወጥነት ችግር ሲታይበት የነበረው ቡድኑ ከመቀመጫ ከተማው ውጪ መጫወቱ ሲያገኝ የነበረውን የሞቀ ድጋፍ ቢያሳጣውም ተጫዋቾቹ ላይ በመጠኑ ሲታይ የነበረውን ጫና ግን እንደሚያቀለው መናገር ይቻላል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑ አንድ ግብ ብቻ መስተናገዱ እና አለመሸነፉ ደግሞ የአዲሱ አሠልጣኝ የቡድን ግንባታን የሚያቀል ሲሆን የማጥቃት አጨዋወቱም በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ሲታይበት የነበረውን የውህደት ክፍተት እየቀረፈ ነው። ነገም ለአዲስ አዳጊው መድን ጠንከር ያለን ፈተና በመለገስ የድሬ ቆይታውን ያሳምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ መድን ከመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ዮሀንስ ውጪ የሁሉንም ተጫዋቾች ግልጋሎት በነገው ጨዋታ ያገኛል። በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀናት ቡድኑን ተቀላቅሎ የነበረው የመሐል ተከላካይ ሀቢብ መሐመድ የወረቀት ጉዳዮቹ ስላለቁለት በጨዋታው መሳተፍ እንደሚችልም ተመላክቷል። ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ ከአምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ኦሴ ማውሊ በተጨማሪ በፋሲሉ ጨዋታ ጉዳት ያስተናገዱት ያሬድ ባየ እና በረከት ጥጋቡ እንዲሁም አደም አባስን መጠቀም አይችልም። ህመም ላይ የነበረው የመስመር አጥቂ ፍፁም ጥላሁን ግን ዝግጁ እንደሆነ ተነግሮናል።

10 ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ካሣሁን ፍፁም በረዳትነት ሀብታሙ መንግስቴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይሳተፋሉ፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ከዓምናው የሜዳ ላይ መጥፎ ውጤቱ በተቃራኒ ለመጓዝ የሜዳ ላይ ጥቅሞቹን ለመጠቀም ከነገው የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ጀምሮ እንደሚጥር ሲገመት ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ባገኘው የአሸናፊነት መንገድ ለመዝለቅ በከተማው ከሚጫወተው ቡድን የሚጠብቀውን ትግል ለማሸነፍ እንደሚታትር ይጠበቃል።

በአዲስ አሠልጣኝ እና አዳዲስ ተጫዋቾች የውድድር ዓመቱን የጀመረው ድሬዳዋ ከተማ በባህር ዳር የነበረው ቆይታ አውንታዊ ውጤት የተገኘበት አልነበረም። እርግጥ በእንቅስቃሴ ደረጃ ያን ያህል መጥፎ ባይባልም በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ያለው አፈፃፀም ግን የወረደ ነበር። በአጥቂ መስመር ላይ የነበረው ውስንነት እየተቀረፈ ቢመስልም በተለይ ውጤትን የማስጠበቅ ችግር ግን ቡድኑ ላይ በጉልህ ይስተዋላል። በመጨረሻዎቹ የሀዋሳ እና ባህር ዳር ፍልሚያዎች ደግሞ ከጨዋታ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ የነበረው ክፍተት እጅ እንዲሰጥ አድርጎታል። ምናልባይ ይህ ክፍተት የሚሻሻል ከሆነ በደጋፊዎቹ እየታገዘ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት እንደሚንደረደር ይታሰባል።

ከኳስ ቁጥጥር በተሻለ ጨዋታን መቆጣጠር እና በአደገኛ ቀጠናዎች ብልጫ መያዝ ላይ እድገት እያሳየ የመጣው ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት ጨዋታዎች የተሻለ ብቃት ካሳየበት የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ማግስት የቀናትም ቢሆን እረፍት መምጣቱ እና የውድድር ከተማ ለውጥ መደረጉ ምናልባት ከነበረበት ጥሩ መንገድ ካላስወጣው የሚገኝበት አቋም ጥሩ የሚባል ነው። የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር እና የሚገኙትን ከመጠቀም በአጠቃላይ ከቀጥተኝነት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች የነበሩበት ቡድኑ አሁን ፎርሙላውን ያገኘ ይመስላል። ወሳኞቹ አጥቂዎችም ግብ እያስቆጠሩለት ስለሆነ ነገም በሚገኝበት ብቃት ባለሜዳውን በመፈተን ወደ ደረጃው አናት በደንብ ለመጠጋት ይጠራል ተብሎ ይጠበቃል።

ድሬዳዋ ከተማ በነገው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ከማይሰለፈው እንየው ካሣሁን ውጪ የሚያጣው ተጫዋች የለም። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ አማካዩ ሮቤል ተክለሚካኤል እና አጥቂው መስፍን ታፈሰን በጉዳት አያሰልፍም።

ምሽት 1 ሰዓት ሲል የሚደረገውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ከረዳቶቹ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ዳንኤል ጥበቡ እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ጋር በመሆን ይመሩታል።

ያጋሩ